You are currently viewing በ24 ሰዓታት ውስጥ 15 ሺህ ናሙናዎችን ለመመርመር አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በ24 ሰዓታት ውስጥ 15 ሺህ ናሙናዎችን ለመመርመር አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

በ24 ሰዓታት ውስጥ 15 ሺህ ናሙናዎችን ለመመርመር አቅዶ እየሰራ ያለው ሚኒስቴሩ ኅብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በመተግበር የዘመቻው ተባባሪ እንዲሆን ጥሪ አቅርቧል፡፡

ከነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ናሙናዎችን በመመርመር የቀጣይ ጊዜያት ሥራዎችን አቅጣጫ ለመወሰን የሚያስችል ዘመቻ በመላ ሃገሪቱ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የወቅቱ የዓለማችን ግንባር ቀደም የጤና ስጋት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በወርሃ ታኅሣሥ በሃገረ ቻይና ከተከሰተ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ20 ሚሊዮን በላይ ደርሷል፡፡ በቫይረሱ ሕይዎታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥርም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ በአንዳንድ የዓለም ሃገራት ደግሞ የቫይረሱን ስርጭት በተወሰነ ደረጃ መግታት ቢችሉም በሕዝቦቻቸው መዘናጋት ምክንያት ወረርሽኙ እንደገና እያገረሸ መምጣቱ እየተነገረ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ቫይረሱ መገኘቱ ከታወቀበት መጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት አምስት ወራት የቫይረሱ ስርጭት እያሻቀበ መምጣቱን መረጃዎቹ ያመላክታሉ፡፡ በኢትዮጵያ የ151 ቀናት የቫይረሱ ስርጭት የቆይታ ጊዜም 509 ሺህ ገደማ የናሙና ምርመራ ተከናውኖ 23 ሺህ 591 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር ዕለታዊ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ መረጃ ያመላክታል፡፡ 10 ሺህ 411 ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ሲያገግሙ 420 ሰዎች ደግሞ ሕይዎታቸውን አጥተዋል፡፡

ባለፉት አምስት ወራት ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ናሙና ምርመራን ደቡብ አፍሪካ ድረስ ልካ ከማስመርመር ጀምራ አሁን በሃገሪቱ 48 የኮሮና ቫይረስ ላቦራቶሪ መመርመሪያ ማዕከላት ሥራ ላይ መሆናቸውን የጤና ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ገልጸዋል፡፡ በሚቀጥሉት ቀናትም ወደ ሥራ የሚገቡ የመመርመሪያ ማዕከላት መኖራቸውን የጠቆሙት ዶክተር ተገኔ ይህም የ24 ሰዓት የመመርመር አቅምን 15 ሺህ እንደሚያደርሰው ገልጸዋል፡፡

ከነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀመሮ በሁለት ሳምንታት 200 ሺህ ናሙና ለመመርመር የሚያስችል ዘመቻ መጀመሩን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ዘመቻው ሁለት ዓላማዎች እንዳሉት ጠቅሰዋል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ በስፋት እየተስተዋለ ያለውን መዘናጋትና ቸልተኝነት መከላከል እና ከዘመቻ ውጤቱ በኋላ በቀጣይ ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች ለመወሰን የሚያስችል መረጃ መሰብሰብ የዘመቻው ዓላማዎች መሆናቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

ራስን ማወቅ ከራስ አልፎ ለቤተሰብ፣ ለማኅበረስብ እና ለሃገር የሚጠቅም በመሆኑ ለዘመቻው ስኬት የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡ በ24 ዓዓታት ውስጥ 15 ሺህ ናሙናዎችን ለመመርመር የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ወይ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዶክተር ተገኔ ካለፈው ሳምንት በፊት በቂ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ መጠናቀቁን ገልጸዋል። ከውስን ቦታዎች በስተቀር በሁሉም የመመርመሪያ ማዕከላት በቂ የህክምና ቁሳቁስ መድረሱንና በቀሪዎቹ ቦታዎች ደግሞ እየተሰራጨ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ናሙናዎችን ወደ መመርመሪያ ማዕከላት ለማድረስ የትራንስፖርት ችግር ይኖራል በሚል ስጋት በየአካባቢው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር የተቋቋመው ግብረ ኃይል ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ ማኅበረሰቡ እድሜያቸው የገፉ እና ተጓዳኝ የጤና ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ከቤት እንዳይወጡ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግላቸውም አሳስበዋል። ሁሉም ከቤት ውጪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሎችን በመጠቀም፣ በተቻለ መጠን አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና እጅን በማፅዳት የዘመቻው ተባባሪ እንዲሆንም ዶክተር ተገኔ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

(አማራ ብዙኃን መገናኛ)

Leave a Reply