You are currently viewing በኢትዮጵያ ከ13 ሚሊየን በላይ ሰዎች የጉበት በሽታ ተጠቂ መሆናቸው ተገለፀ!

በኢትዮጵያ ከ13 ሚሊየን በላይ ሰዎች የጉበት በሽታ ተጠቂ መሆናቸው ተገለፀ!

August 10 2021, Doctors Online Ethiopia

 

በኢትዮጵያ የጉበት በሽታ ስርጭት 11 በመቶ የደረሰ ሲሆን ፣ ይህም ከኤች አይ ቪ ስርጭት በላይ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የኤች አይቪ እና ቫይራል ኤፔታይተስ ፕሮግራም አስተባባሪ ወይዘሮ ምርቴ ጌታቸው ህብረተሰቡ ራሱን ከዚህ ቫይረስ ሊጠብቅ እንደሚገባ አሳስበው ፣ የሄፓታይተስ በሽታ አሁን ላይ ከአለም በገዳይነቱ በ2ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሽታው በስፋት ከተሰራጨባቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ፣ በ2017 በተሰራ ጥናት መሰረት 9 ነጥብ 4 በመቶ በሄፓታይተስ ቢ ፣ 3 ነጥብ 1 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ሄፓታይተስ ሲ ተጠቂ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ከ13 ሚሊየን በላይ ሰዎች የጉበት በሽታ ተጠቂ ናቸው፡፡

በአጠቃላይ 5 አይነት የጉበት በሽታ ቫይረስ አይነቶች ሲኖሩ እነዚህም ሄፓታይተስ ኤ ፣ ቢ ፣ ሲ ፣ ዲ እና ኢ ይባላሉ፡፡ በስፋት በሽታን በማምጣት እና አስጊ በመባል የሚታወቁት ቢ እና ሲ መሆናቸውን ወ/ሮ ምርቴ ጌታቸው በተለይም ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል፡፡

የአለም ጤና ድርጅት በአንድ አገር የጉበት በሽታ ስርጭት ከ8 በመቶ በላይ ከሆነ ክትባቱን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል መውሰድ እንዳለበት የሚያዝ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የጉበት በሽታ ስርጭት እየተስፋፋ ቢሆንም ክትባቱን በነጻ ማቅረቡ አዳጋች መሆኑ ይነገራል፡፡

ሆኖም ከእናት ወደልጅ ያለው ስርጭት ከፍተኛ በመሆኑ አዲስ የሚወለዱ ልጆች የጉበት በሽታ መከላከያ ክትባት መሰጠት ለመስጀመር ቅድመ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ ከ700 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች ክትባት መሰጠቱም ተጠቁሟል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች በሄፓታይተስ በሽታ ህይወታቸውን እንደሚነጠቁም መረጃዎች ያመለክታሉ።

በትግስት ላቀው
Via: ዳጉ ጆርናል

 

 

Join Doctors Online Ethiopia on Telegram

 

Leave a Reply