You are currently viewing ሀሰተኛ መድሃኒቶችን ከእውነተኞች እንዴት መለየት እንችላለን?

ሀሰተኛ መድሃኒቶችን ከእውነተኞች እንዴት መለየት እንችላለን?

 

June 27 2021, Doctors Online Ethiopia

 

መግቢያ

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ሀሰተኛ መድሀኒቶችን ለመድሃኒት ቤቶች የሚያቀርቡ እንዲሁም በህገወጥ መንገድ መድሃኒቶችን የሚቸበችቡ ግለሰቦችን እዚህም እዛም ማየት የተለመደ ሆኗል:: ለአብነት ያክል ከየት እንደመጡ እና በምን መንገድ እንደመጡ ወይም ማን እንዳመረታቸው በውል የማይታወቁ መድሀኒቶች እንደተራ እቃ በየቴሌግራም ግሩፖቹ እንዲሁም ብዙ ተከታይ ባላቸው ቻናሎች ሳይቀር ያለሀፍረት ሲተዋወቁ ይስተዋላሉ:: ቅርብ ጊዜ በሀገራችን በተሰራ ጥናት በሀገሪቷ ውስጥ ከሚሸጡ መድሀኒቶች 8 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ከአስፈላጊው የጥራት ደረጃ በታች እንደሆኑ ተደርሶበታል::

ከዚህ በታች ያሉት መንገዶች ሀሰተኛን ከእውነተኛ መድሀኒት ሙሉ ለሙሉ ለመለየት ባያስችሉም ነገር ግን ፈዋሽነት የሌላቸው አልያም ጎጂ የሆኑ መድሀኒቶችን በተወሰነ መልኩ ለመለየት ያግዛሉ::

በድንገተኛ ጊዜ ሚጠብቅ ፈጣሪ ብቻ ቢሆንም ፤ ግን ጊዜ ሲኖር እና ረጋ ብሎ ማሰብ ሲቻል እኚህን ነገሮች ልብ ማለት መልካም ነው:-

1. የመድሀኒቱ ዋጋ እንዴት ነው? :-

 

የመድሀኒት ዋጋ ከፋርማሲ ፋርማሲ ይለያያል:: ጎን ለጎን ያሉ ፋርማሲዎች እንኳን አንድ አይነት መድሃኒትን ለየቅል በሆነ ዋጋ ሊሸጡ ይስተዋላሉ:: ሆኖም ግን የትም በሌለ እርካሽ ዋጋ መድሀኒት ሲያገኙ ሁልጊዜ ልብ ይበሉ ፤ መድሀኒቱ ለምን እንደረከሰ ሳያጣሩ ከኪሶት ገንዘብ አያውጡ::

 

2. የመድሃኒቶቹ ገፅታ ምን ይመስላል?

 

በአለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሰረት መድሀኒቶች ላይ ልብ ሊባሉ የሚገባቸው የአካላዊ የፅታዎች

– ብዙ የደቀቁ ዱቄታማ ዝቃጮች

– የተሰባበሩ ኪኒኖች (ባለሞያ ለአጠቃቀም እንዲመች ሆን ብሎ ያልሰባበራቸው)

– ክሪስታል የመሰሉ ገፅታዎች በመድሃኒቶቹ ላይ ወይም በመድሃኒቱ እቃ ላይ ካሉ

– በጣም የለሰለሱ ወይም በጣም የጠነከሩ መድሃኒቶች

– ቀለማቸውን የለቀቁ አልያም ገፅታቸው ላይ በአድ ነገር የሚታይባቸው ወይም እንደማበጥ ያሉ ኪኒኖች

ከላይ ከተጠቀሱ ነገሮች መሀል አንዱን መድሃኒቶቹ ላይ ካስተዋሉ ቢችሉ አይጠቀሟቸው::

 

3. የመድሀኒቱ ውስጠኛ ማሸጊያ ክፍት ነው ወይ?

 

መድሃኒቱ የታሸገበት ካርቶን ሳይሆን የመድሀኒቱ ውስጠኛ ማሸጊያ ክፍት ሆኖ መድሀኒቱ ተጋልጦ ካገኙት መድሃኒቱን አይግዙት:: ይህ መድሃኒት እውነተኛም ሆነ ሀሰተኛ ለጤናዎ ጠንቅ ይዞ ሊመጣ ይችላል:: ነገር ግን ይህ በሀኪሙ ትዕዛዝ መሰረት ለመቀነሻ በተዘጋጀ እቃ እየተቀነሱ በህጋዊ ፋርማሲ ውስጥ የሚሸጡ መድሃኒቶችን አያካትም::

 

4. መድሀኒቱን የሸጠሎት ማን ነው? 

 

ማንም ሰው በተለይም የጤና ባለሞያ ያልሆነ ወይም የመሸጫ ፍቃድ የሌለ ሰው እጅ በእጅ መድሀኒት ልሽጥልዎ ቢልዎ አይቀበሉ::

 

5. የመድሃኒቱ ማሸጊያ ላይ ያሉትን ፅሁፎች ከቻሉ በግርድፉ ይዯዋቸው::

ግልፅ የሆነ የስፔሊንግ ስህተት ፣ ያልተለመደ የፅሁፍ አይነት (font) እና ሌሎች ፍንትው ብለው የሚታዩ የህትመት ችግሮች ካዩ ልብ ይበሉ::

ይህን መለየት ከከበዶት እቤት ካሎት ያለቀ መድሀኒት እቃ ጋር ማስተያየት  ሊጠቅሞት ይችላል::

6. ኤክስፓየሪ ዴቱን ይዩት:-

 

መድሀኒቱ ኤክስፓየሪ ዴት ከሌለው ወይም ቀኑ ካለፈ ሌላ ሰው ተጠቅሞ ጉዳት ሊደርስበት ስለሚችል ለሚመለከታቸው አካላት ያሳውቁ::

7. አለርጂዎች እና ያልተጠበቁ የጎንዮሽ ጉዳቶች :-

 

መድሀኒት ሲታዘዝልዎ ስለጎንዮሽ ጉዳታቸው ሀኪሙን መጠየቅ በጎ ልማድ ነው:: ማንኛውም መድሃኒት ወስደው ሀኪም ከነገሮት ወይም ከተአማኒ የኦንላይን መረጃ ምንጮች ላይ ከተጠቀሰው ውጪ የሆኑ የጤና እክሎች ካጋጠምዎ በአስቸኳይ የወሰዱትን መድሀኒት ይዘው ወደሀኪም ቤት ይሂዱ::

8. የኦንላይን መድሀኒት አምራች ማረጋገጫዎችን መጠቀም

 

ከውጪ የገቡ መድሃኒቶችን ከተጠራጠሩ እንደ Pharmasecure (pharmasecure.com) ያሉ የኦንላይን መድሀኒት አምራች ማረጋገጫዎች ላይ የመድሃኒቱ ፓኬት ላይ ያለን ልዩ ኮድ በመጠቀም ማረጋገጥ ይችላሉ ::

Leave a Reply