You are currently viewing እነዚህን ምልክቶች ካዩ የስኳር በሽታ ምርመራን ቢያደርጉ ይመከራል ‼️

እነዚህን ምልክቶች ካዩ የስኳር በሽታ ምርመራን ቢያደርጉ ይመከራል ‼️

የስኳር በሽታ

መግቢያ

 

የስኳር በሽታ በአለማችን በስፋት ከሚገኙ የረጅም ጊዜ ህመሞች አንዱ ሲሆን የኩላሊት ድክመት በቀዳሚነት በማስከተል ይታወቃል።

በሰውነታችን ያሉ ሁሉም ሴሎች ግሉኮስን ጉልበት ለማማንጨት ይጠቀማሉ። ታዲያ ሴሎች ስኳርን ወይም ግሉኮስን ሀይል ለማማንጨት ይጠቀሙበት ዘንድ ወደ ውስጣቸው መግባት አለበት።ግሉኮስ ወደ ሴሎች ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ በር ተቆጣጣሪ ኢንሱሊን የተባለ ሆርሞን አለ። ታዲያ ይህ ኢንሱሊን ሳይኖር ወይ ደሞ ኖሮም በር መክፈት ሲያቅተው ግሉኮስ ወደ ሴሎች ሳይገባ ይቀራል። ይህም የደም የግሉኮስ መጠንን ከፍ ያደርገዋል። ይህንንም የስኳር በሽታ እንለዋለን።

አንድ ሰው ምግብ ሳይበላ(ፆሞ) በተደጋጋሚ ስኳሩ ከ126 በላይ ከሆነ ስኳር አለበት ይባላል። ሌሎች ዘዴዎችም አሉ።

 

3 ዋናዋና የስኳር ዓይነቶች

 

1. የኢንሱሊን እጥረት (type 1 diabetes)

ይህ የሚከሰተው የገዛ የራስ የመከላከያ ሴሎች ኢንሱሊን የሚያመነጩ ሴሎችን ሲገድሉ ነው። የዚህ ህመም ተጠቂ ለመኖር ኢንሱሊን መውሰድ አለበት። በብዛት በልጅነት ይጀምራል።

2. በቂ ኢንሱሊን እያለ የሚከሰት (type 2 diabetes)፦ ይህ ልክ በር እንደማይከፍት ቁልፍ ነው። በቂ ኢንሱሊን ቢኖርም የሴሎችን የጉሉኮስ በር አይከፍትም።ነገር ግን በጊዜ ሂደት የኢንሱሊኑም መጠን ሊቀንስ ይችላል። ይህ በብዛት ውፍረትን ተከትሎ እድሜ እየጨመረ ሲመጣ ይከሰታል። የተለያዩ የአኗኗር ዘይቤዎችን በማስተካከል፣ በሚዋጡ መድሀኒቶችና በኢንሱሊን ሊታከም ይችላል።

3. የእርግዝና ወቅት ስኳር ፦ይህ ከእርግዝና በፊት ያልነበረና ከወሊድ በኋላ የሚጠፋ ሲሆን ነገርግን እነዚህ ሴቶች በኋላ ላይ በሁለተኛው ዓይነት የስኳር በሽታ የመያዝ ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።

 

የስኳር በሽታ ምልክቶች

 

ወደ ነጥቤ ስገባ የሚከተሉት 10 ምልክቶች ካሉቦት ስኳር ሊሆን ስለሚችል በአፋጣኝ ይመርመሩ(ስኳሮትን):-

1ኛ፦ብዙ ጊዜ መሽናት ፡ አሁንም አሁንም በቀን በሌሊት የሚመጣ ሽንት የስኳር ምልክት ሊሆን ይችላል። ለሽንት ማታ ከ6 ጊዜ በላይ የሚነሱ ከሆነ ስኳርዎ መታወቅ አለበት።ብዙ ጊዜ መሽናት የፈሳሽ መጠንዎን በመቀነስ የድካም ስሜት ያስከትላል።

2ኛ፦ ከፍተኛ የውሃ ጥም፦ ብዙ ይጠጣሉ ግን ብዙ ስለሚሸኑ ቶሎ ቶሎ ይጠማዎታል። የማያቋርጥ አዙሪት

3ኛ፦ያልታሰበበት የክብደት መቀነስ ፡ ሳያስቡና ሳይፈልጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ የክብደት መቀነስ ካጋጠሞት ስኳርዎን ቼክ ማድረግ ያስፈልጋል።ሴሎች ጉሉኮስ መጠቀም ስላልቻሉ ይህ ይከሰታል።

4ኛ፦ ከፍተኛ የድካም ስሜት ፡ይህ አንድም የሰውነት ፈሳሽ በሽንት መልክ በመውጣቱ አልያም ሴሎች ግሉኮስን ለጉልበት ባለመጠቀማቸው ይከሰታል።

5ኛ፦ የረሀብ ስሜት፦ከሌላ ጊዜ የበለጠ እየበሉ ቶሎ ቶሎ መራብ የስኳር ምልክት ሊሆን ይችላል ።

6ኛ፦ ተደጋጋሚ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን ፦ ይህም በስኳሩ የተነሳ የሰውነት የመከላከል አቅም ስለሚዳከም ነው። በተጨማሪም ተደጋጋሚ የፈንገስ ኢንፌክሽን በተለይ በሴቶች ሲከሰት የስኳር ምልክት ሊሆን ስለሚችል መመርመር ያስፈልጋል።

7ኛ፦ቁስል በቶሎ ያለመድረቅ፡ ይህም ከሰውነት መከላከያ አቅም ማነስ ይያያዛል።

8ኛ፦ የቆዳ መጥቆር ፦ የብብትና የአንገት አካባቢ የቆዳ መጥቆር የኢንሱሊን ችግር መኖሩን ያሳያል። ይህም የስኳር ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው። ስኳር ቼክ ማድረግና ክብደት መቀነስ ያስፈልጋል።

9ኛ፦ የእጅና እግር መደንዘዝና ማቆጥቆጥ። ይህ ለረጅም ጊዜ ሳይታወቅ የቆየ ስኳር የነርቭ ጫፎችን ሲጎዳ የሚፈጠር ነው

10ኛ፦ የአይን ብዥታ፡ በጊዜ ከሆነ ስኳሩን ሲታከሙት የሚጠፋ ነው። በጣም ከዘገየ ግን ለዓይነ ስውርነት ይዳርጋል።

ጤናማ አመጋገብና እንቅስቃሴ በማድረግ እራሳችንን ከስኳር በሽታ እንጠብቅ።

✍️ፀሀፊ :- በዶክተር ሸምስ (የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ሐኪም)

 

For More Healthcare Articles Click Here

To Get our Latest healthcare articles Alerts go Join Our Telegram Channel

 

Leave a Reply