You are currently viewing አብዝቶ የመጠራጠር የስብእና ህመም‼️

አብዝቶ የመጠራጠር የስብእና ህመም‼️

May 2021, Dr Yonas Lakew

እንደዚህ አይነት ስብእና ያላቸው ሰዎች በብዛት ‘ሲሪየስ’ እና ለራሳቸው የተጋነነ ግምት የሚሰጡ ሲሆኑ ከሁሉም ሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በንቃት ነው የሚከታተሉት። በሌሎች ሰዎች ንግግር እና ድርጊት የተደበቀ እነሱን ሊጎዳ የሚችል ሊኖረው እንደሚችል ስለሚያስቡ ሰውን ማመን ይከብዳቸዋል። ስነ ልቦናዊ መሰረቱ አሉታዊ ሀሳቦቻቸውንና ስሜቶቻቸውን መቀበል አለመቻል ነው። በራሳቸው የማይቀበሏቸውን ስሜትና ሀሳቦች በሌሎች ላይ ስለሚስሉ ሌሎች ሰዎችን ይፈራሉ።

ሀዘን ወይም ሀፍረት እንደሚሰማው ሰው አይናቸውን አይሰብሩም። ወይም እንደፈራ ሰው ወደ ጎንም አያዩም። በብዛት የሚያዩት ‘በቆሪጥ’ ነው። ሀዘን ብዙ ጊዜ አይስተዋልባቸውም። ምክኒያቱ ደግሞ ሀዘን ቢያንስ በሁለት መንገድ ሊፈጠር ይችላል። አንደኛው በራስ በመናደድ ነው። የበዛ ተጠራጣሪ ስብእና ያላቸው ሰዎች አሉታዊ ነገሮችን በራሳቸው ላይ ስለማይቀበሉ በራሳቸው ሊናደዱ አይችሉም። ሁለተኛው ሀዘን የሚፈጥረው የሚፈልጉትን ነገር ማጣት ነው። አነሱ ያላቸው “ምናልባት ባጣውስ?” የሚል ጥርጣሬ ነው እንጂ ቁርጡ የለየለት ጉዳይ አይደለም። ስለዚህ ከሀዘን ይልቅ በብዛት የሚሰማቸው ስሜት ጭንቀት፣ ፍርሀትና ምቀኝነት ነው። ምቀኝነትን እንደሌሎቹ አሉታዊ ስሜቶች በራሳቸው መቀበል ስለማይችሉ “ሰዎች ይመቀኙኛል!” ብለው ይገልፁታል።

እንደዚህ አይነት ስእብና ያላቸው ከሌሎቹ የስብእና ህመሞች አንፃር በብዛት አልተጠኑም። ምክኒያቱ ግልፅ ነው። አንደኛ ህመሙን ስለማይቀበሉት ሲሆን ሁለተኛው ቢቀበሉት እንኳ “ለምንድነው የምታጠኑት?” ወይም “እኔን ለምን መረጣችሁን?” የሚል ጥርጣሪ ስለሚፈጠርባቸው ነው። የበዛ ተጠራጣሪ የሆኑ ሰዎች በሁለት ስነ ልቦናዊ ምክኒያቶች ስልጣን ላይ ይወጣሉ። አንደኛው ስልጣን ላይ ሲሆኑ በግልፅ የሚቃረኗቸው ሰዎች ይኖራሉ። ይሄ “ምናልባት?” እያሉ በምናብ ከመጨናነቅ ይቀላል። ሁለተኛው ስልጣን ላይ ከሆኑ ‘ሊጎዷቸው’ የሚችሉት ሰዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ይችላሉ።

የበዛ ተጠራጣሪነት ያላቸው ሰዎች ወደ ህክምና አይመጡም። ከነሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ላይ የሚሳድሩት ጫና ግን ቀላል አይደለም። ምን አይነት አስዳደግ ወደ የበዛ ተጠራጣሪ ስብእና እንደሚመራ በሌላ ጊዜ አቀርባለሁ።

አብዛኞቹ ሀሳቦች ከ Psychoanalytic diagnosis: understanding personality structure in the clinical process. Nancy McWilliams የተወሰዱ ናቸው።

መልካም ጊዜ!
ዶ/ር ዮናስ ላቀው

 

For More Healthcare Articles Click Here 

To Get Alerts of Latest Healthcare Articles Join Our Telegram Channel 

Leave a Reply