መግቢያ
የግብረ ስጋ ግንኙነት ( ሴክስ) ለሰው ልጅ እጅግ አስፈላጊ የህይወት አካል ነው:: በዋነኝነት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚታወቁ የሴክስ ጥቅሞች የመራቢያ መንገድ መሆኑ እና የደስታ ምንጭ እንዲሁም የፍቅር መገለጫ መሆኑ ነው:: ነገር ግን ከዚህ ሁሉ ባለፈ በወንድ ልጅ ብልት እና የሴት ልጅ ብልት በመሰርሰር የሚደረግ የግብረስጋ ግንኙነት ጥቅሞች በሁሉም የህይወት ክፍሎች ላይ የሚንፀባረቁ ናቸው:: እነዚህ ጥቅሞች በአካላዊ ፣ በአእምሮአዊ ፣ በስነልቦናዊ እና በማህበረሰባዊ ጤንነታችን ላይ ጎልተው ይንፀባረቃሉ::
ነገር ግን ሰዎች ጤናማ የግንኙነት ህይወት እንዳይኖራቸው የሚያደርጉ በርካታ የጤና እክሎች አሉ:: ከእነዚህ መካከል በዚህ ፅሁፍ ሁለቱን እንዳስሳለን::
የግብረስጋ ግንኙነት ጥቅሞች በዝርዝር
1. የልብና የደም ዝውውር ጤንነትን ለመጠበቅ
በተለያዩ ጊዜያት በሴክስ ዙርያ የተደረጉ በአለም ዙርያ ባሉ ተመራማሪዎች የተገመገሙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የግብረ ስጋ ግንኙነት እራሱን የቻለ አካል ብቃት እንቅስቃሴ ነው:: ይህም ሴክስ የሚከተሉትን የጤና በረከቶች እንዲሰጥ ያስችለዋል::
- የደም ግፊትን መቀነስ
- ጡንቻዎችን ማጠንከር
- ካሎሪ ማቃጠል
- የልብን ጤና መጠበቅ
- የስትሮክ ፣ የከፍተኛ የደም ግፊት እና የልብ በሽታ የመፈጠር እድልን ይቀንሳል::
2. የሰውነት የበሽታን መከላከል አቅምን ያጠነክራል::
በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎች ላይ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በፍቅር ህይወት ውስጥ ያሉ በሳምንት ከ1 – 2 ጊዜ የግብረ ስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ከፍ ያለ ኢሙኖግሎብዩሊን ኤ ( immunoglobulin A) የተሰኘ በሽታን ለመከላከል የሚያስችል ፀረእንግዴን በምራቃቸው ውስጥ ይይዛሉ::
ነገር ግን በሳምንት ከሶስቴ በላይ የግብረስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ሰዎች አዘውትረው የግብረስጋ ግንኙነት ከማያደርጉ ሰዎች ጋር ተመሳሳይ የኢሙኖግሎብዩሊን ኤ ፀረ እንግዴ መጠን ይኖራቸዋል::
በተጨማሪም ጥናቶች እንደሚያሳዩት የአዕምሮ ውጥረት እና ጭንቀት ሴክስ በዚህ ረገድ የሚኖሪትን ጥቅሞች ሊያሳጣው እንደሚችል ያሳያሉ::
3. የተሻለ እንቅልፍ
በሌላ ስሙ የፍቅር እና የቅርርብ ሆርሞን ተብሎ የሚጠራው ኦግዚቶሲን እና የደስታ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርገው ኢንዶርፊን ሆርሞን በግብረ ስጋ ግንኙነት የደስታ ጣራ (Orgasm) ጊዜ መለቀቃቸው እንቅልፍን የማስተኛት ባህሪ ይኖራቸዋል::
ሴክስ የተሻለ እንቅልፍ ማስተኛት መቻሉ ደግሞ
የሰውነት በሽታን የመከላከል አቅምን እንዲጨምር ፣ እድሜን እንዲያረዝም ፣ የእረፍት ስሜት እንዲሰማ በማድረግ ረገድ እንዲሁም ለቀኑ የበለጠ ጉልበት እንዲኖረን በማድረግ የራሱን ሚና ይጫወታል::
4. የእራስምታትን ማስታገስ
አንድ ሌላ ጥናት እንዳሳየው ሴክስ ማድረግ ለማይግሬን እና ክለስተር እራስምታቶች ከመለስተኛ እስከሙሉ ለሙሉ ማስሻል የሚደርስ ጥቅም ሊኖረው እንደሚችል አሳይተዋል::
በእራስ ምታታቸው ወቅት ንቁ የግብረስጋ ግንኙነት ህይወት ከነበራቸው የጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በማይግሬን እራስ ምታታቸው ላይ መሻሻል እንዳዩ ተናግረዋል::70 በመቶ የሚሆኑት ከመለስተኛ እስከ ሙሉ ለሙሉ የማይግሬን እራስምታት መሻል አሳይተዋል::
በተመሳሳይ ለክለስተር እራስምታት ደግሞ 37 በመቶዎቹ መሻሻል ሲያሳዩ 91 በመቶዎቹ ከመለስተኛ እስከ ሙሉ ለሙሉ የክለስተር እራስምታት መሻል አሳይተዋል::
የግብረስጋ ግንኙነት ጥቅሞች በፆታ ተከፍለው::
ለወንዶች
የፕሮስቴት ካንሰር
ቅርብ ጊዜ የተካሄደ የጥናት ግምገማ እንዳመላከተው አዘውትረው በወንድ ብልት የሴት ብልትን በመሰርሰር የሚደረግ ግብረስጋ ግንኙነት የሚያደርጉ ወንዶች ከማያደርጉት አንፃር አነስተኛ በፕሮስቴት ካንሰር የመያዝ እድል ይኖራቸዋል::
ከዚው ጋር በተገናኘ አንድ ጥናት እንዳገኘውም በሳምንት በአማካይ ከ 4.6 -7 ጊዜ የዘር ፍሬያቸውን የሚረጩ ወንዶች በሳምንት 2.3 ጊዜ እና ከዚያ በታች ከሚረጩት ወንዶች አንፃር ከ70 አመት ልደታቸው በፊት የፕሮስቴት ካንሰር አለባችሁ የመባል እድላቸው በ36 በመቶ ይቀንሳል::
እድሜን ማስረዘም
ሴክስ የወንዶችን እድሜ ሊያስረዝም ይችላል:: ተሳታፊዎቹ ላይ የአስር አመት ክትትል በማድረግ የተሰራ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በሳምንት ሁለቴ ወይ ከዚያ በላይ የግብረ ስጋ ግንኙነት የደስታ ጣራ (Orgasm) ላይ የሚደርሱ ወንዶች በሳምንት ከ2 ጊዜ ያነሰ ከሚደርሱት አንፃር የመሞት እድላቸው በ50 በመቶ ይቀንሳል::
የዘር ፍሬ ጥራትን መጨመር
በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰሩ ጥናቶች ባገኙት ውጤት እርስ በእርሳቸው ቢጣረሱም ፤ የጨመረ (ንቁ) የግብረስጋ ግንኙነት ህይወት ያላቸው ወንዶች የዘር ፍሬ ጥራታቸው ሊጨምር ይችላል::
ለሴቶች
የግብረስጋ ግንኙነት ጣራ ላይ መድረስ የደም ዝውውርን ከመጨመር በተጨማሪ ተፈጥሮአዊ የህመም ማስታገሻ ኬሚካሎች እንዲለቀቁ ያደርጋል::
ለሴቶች የግብረስጋ ግንኙነት ማድረግ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይሰጣል :-
- የተሻለ የሽንት መቆጣጠር እንዲኖር ( Bladder control )
- የሽንት ማምለጥን (Urinary Incontinence) መቀነስ
- የወር አበባን እንዲሁም ከወር አበባ በፊት የሚከሰት ቁርጠትን ማስታገስ
- መውለድ የመቻል አቅምን (Fertility) ያሻሽላል
- የፔልቪስ ግድግዳ ጡንቻዎችን ጥንካሬ መጨመር
ሴክስ የፔልቪስ ግድግዳ ጡንቻዎችን ጥንካሬ መጨመሩ በግብረ ስጋ ግንኙነት ወቅት የሚኖርን የህመም ስሜት ይቀንሳል በተጨማሪም የብልት ውስጠኛው ክፍል ወደውጪ የመውጣት በሽታን (vaginal prolapse) ይከላከላል::
የሴክስ ጥቅሞች ብዙ እና ከዚህ በላይ ሊተነኑ የሚችሉ ናቸው:: ነገር ግን ለጊዜው እዚህ ላይ ቋጭተናቸው ወደ ሴክስ እክሎች እናምራ::
የግብረስጋ ግንኙነት ተግዳሮቶች
1. ስንፈተ ወሲብ
ስንፈተ ወሲብ ወይም የብልት መልፈስፈስ ችግር የሚሊየኖች ወንዶች ችግር መሆኑ ይታወቃል። ይህ ቢሆንም ይህን ችግር በተለያየ መንገድ መቅረፍ ይቻላል። አብዛኛዎቹ ወንዶች ችግሩን የሚያባብሱት ስለችግራቸው ለማንም ሳያማክሩ በውስጣቸው አምቀው በመያዛቸውና ይህም ለጭንቀትና ውጥረት እንድሁም ፍራቻ ምክንያት በመሆኑ ነው። ከዚህ ችግር ለመውጣት የመጀመሪያው ቁልፍ መንገድ በግልፅ ስለችግሩ ከጤና ባለሙያ ጋር መነጋገር ነው። ይመኑ። ችግረዎት የሚፈታ ነው።
እስከ አሁን ባለው መረጃ በአለም ላይ 30 ሚሊዮን ወንዶች የስንፈተ ወሲብ ችግር አለባቸው። ስንፈተወሲብ ስንል የወንድ ልጅ ብልት ለግብረስጋ ግንኙነት ብቁ ሆኖ አለመገኘት ማለት ነው። ይህ ችግር ደግሞ መፈታት አለበት። ይፈታልም። ካልተፈታ ስነ-አእምሮአዊ ጠባሳው ከባድ ስለሆነ።
• ይህ ችግር ካለብዎ ችግሩ የርስዎ ብቻ አይደለም። የሚሊየኖች ነው። ከችግሩ ለመውጣት በግልፅነት የጤና ባለሞያ ያናገሩ አብዛኛዎቹ ከዚህ ችግር ወጥተዋል። ለመውጣት ያልሞከሩት ደግሞ እዛው ናቸው። እርስዎስ ምን ያህል ግልፅ ነዎት? የት ነው ያሉት?
እስኪ በሚከተሉት አስር ጥያቄዎች እንጀምርና እንቀጥላለን።
1. ያጨሳሉ?
ካጨሱ ያቁሙት። ማቆም ከባድ መሆኑን ብንረዳም ረጫሽ ከሆኑ ከዚህ ችግር ለመጣዉጣት አይችሉም። በሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን ብልት እንድወጠር የሚያደርጉትን የደም ቱቦዎች ያጨማድዳቸዋል። ይህም ብልት በደም ተሞልቱ መጠኑ እንዳይጨምርና እንዳይጠነክር ይዳርገዋል።
2. አመጋገበዎት እንደት ነው?
አመጋገብ ትልቅ ተፅእኖ ያሳድራል። የኮሌስትሮል መጠንን የሚጨምር እንዲሁም ክብደትን የሚጨምሩ ምግቦች ለስንፈተወሲብ አጋላጭ ናቸው። ሰው በራሱ ውፍረት ስንፈተ ወሲብን ያመጣል። ስለዚህ ጤናማ ምግቦችን ይመገቡ። ጥራጥሬ፡ ፍራፍሬ፡ ቅጠላቅጠል፡ ማርና ሌሎች
3. አልኮል ያዘወትራሉ?
አልኮል ከመጠን ሲያልፍ ድብርት ያመጣል። ፆታዊ ስሜትንም ይገላል። ስለዚህ ይቀንሱ። ይተውት።
4. በየቀኑ የአካል እንቅስቃሴ ያደርጋሉ?
በቀን ከ20-30 ደቂቃ ስፓርታዊ እንቅስቃሴ ቢያደርጉ የራስመተማመንዎን ከመጨመረዎ በላይ ወደብልት የሚሄደው የደም መጠን እንድጨምር ያደርጉታል።
5. በህይዎተዎ ጭንቀት፡ ውጥረትና ፍራቻ አለበዎት?
እነዚህ ችግሮች ካሉ በፆታዊ ግንኙነት ውጤታማ ስለማይሆኑ ያስወግዱ። ይቀንሱ።ካስፈለገም የስነልቦና ሀኪምን ያናግሩ::
6. ሌላ የጤና ችግር እንደሌለበዎት አረጋግጠዋል?
የጤናዎትን አጠቃላይ ሁኔታ ይወቁ። የችግሩ ምንጭ ሌላ የጤና ችግር ሊሆን ስለሚችል አጠቃላይ የጤና ምርመራ ያድርጉ።
7. ከትዳር አጋር ወይም ጎደኛዎ ጋር ስለ ችግሩ ተወያይተዋል?
ይህን ችግር ደብቀው ሊቀርፉት ስለማይችሉ በግልፅ ተነጋግረው በተቃራኒ ፆታ ፆታዊ አነሳሽነት ችግሩን ለመቅረፍ መሞከር ጥሩ ነው። በኩርፊያና ንትርክ ችግሩ አይቀረፍም።
8. የራስዎን የSex ህይዎት ከሌሎች ጋር ለማወዳደር ይሞክራሉ?
ይህ የበታችነት ስሜትን ስለሚፈጥርበዎት አያስቡት። ውጤታማም አያደርገዎትም።
9. የጤና ባለሙያ አማክረዋል?
ካላማከሩ ሳይዘገዩ ያማክሩ።
10. የወሲብ ግንኙነት አይሳካልኝም ብለው ያስባሉ?
እንዲህ ካሰቡ ተሳስተዋል።
ስንፈተ ወሲብ ለምን ይከሰታል?
• በቂ የሆነ የደም ፍሰት ወደ ብልት ሳይሄድ ሲቀር
• ብልትን የሚቆጣጠረው ነርቭ ላይ ችግር ካለ
• በግንኙነት ሰአት ጭንቀት፡ ፍራቻና ውጥረት ካለበዎት
• ስሜትዎ የሚዘበራረቅ ከሆነ
• የደም ቱቦ መጥበብ ፣ የልብ ችግር ፣ ከፍተኛ ደም ግፊት ፣ከፍተኛ ስኳር መጠንና ውፍረት ካለ
• የተለያዩ መድሀኒቶች የጎንዮሽ ተፅእኖ
ከላይ ከዘረዘርናቸው ለክስተቱ ከሌሉ ችግሩ ስነ-አእምሮአዊ ነው ማለት ነው። መቼና ለምን ስንፈተወሲብ እንደሚፈጠር ካወቅን በቀላሉ ማካም ይቻላል።
• ፆታዊ ግንኙነት ስሜት ሲፈጠር ነርቭ ኬሚካል ወደ ብልት ይለቃል። በዚህ ወቅት ብልት ውስጥ ያሉ የደም ቱቦዎች ይሰፋሉ። በውስጣቸውም ብዙ ደም ያከማቻሉ። ይህን ጊዜ ብልት ይወጠራል። ይጠነክራል። ችግሩ ካለ ግን ይህ አይሆንም።
• የብልት መልፈስፈስ ወይም ስንፈተወሲብ ከሚከተሉት የጤና ችግሮችም ሊሆን ስለሚችል አጠቃላይ የጤና ምርመራ ማድረግ እጅግ ጠቃሚ ነው። ከልብ ቾግር፡ ከስኳር በሽታ፡ ከውፍረት፡ ከከፍተኛ ደም ግፊት፡ ከነርቭ ችግር፡ ከደም ቱቦ መጥበብ፡ ከሆርሞንና ሌሎችም ችግሮች አኳያ ሊሆን ይችላል። እንደቀላል ይህን ችግር ዝም ካሉት ለራስዎት የሚሰጡትን ክብር ይቀንሳል፡ በራስ መተማመንን ያወርዳል፡ በትዳርና ፍቅረኛ መሀል ክፍተትን ይፈጥራል።
አጋላጭ ሁኔታዎች
• የእድሜ መጨመር ወይም እርጅና
• የስኳር ታማሚ መሆን
• ከፍተኛ ደም ግፊት
• የልብ ችግር
• የኮሌስትሮል መጠን መጨመር
• ማጤስ
• አልኮል ጠጭ መሆን
• ወፍራም መሆን
• የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ
• የመድሀኒቶች ሱሰኛ መሆን
• አድሜ መጨመር ስንል ለሁሉም ማለት አይደለም። ብዙ ወንዶች እስከ 100 አመት አካባቢ ውጤታማ ናቸው።
አስቡ ከላይ የዘረዘርናቸው ችግሮች ካልሆኑስ? አይጠራጠሩ የችግሩ ምክናየት ስነ-አእምሮአዊና የስሜት ችግር የፈጠረው ነው። ትክክለኛ የግብረ ስጋ ግንኙነት አእምሮ፡ ስሜትና አካላችን ተናበው በአንክሮ የሚከወን ነው። በሩጫ፡ በፍራቻና በውጥረት በውክቢያ የሚሆን አይደለም።
ግንኙነት የሚከተሉት ካሉበት ስነአእምሮአዊ ችግሮችን ተላብሶአል ማለት ነው።
• ድብርት
• ጭንቀት
• ውጥረት
• ከትዳር አጋር ወይም ፍቅረኛ ጋር ፀብ ካለ
• በህይዎት ውስጥ እረፍት ከሌለ
• በማህበራዊ ህይዎት፡ በባህልና እምነት የሚደርስ ተፅእኖ መኖር
• ለግብረ ስጋ ግንኙነት ብቁ አይደለሁም የሚል እምነት ቀድሞ መኖር
የዚህን ችግር ምንጭ ለማወቅ ከላብራቶሪ ምርመራዎች ጀምሮ የተለያዩ በመሳሪያዎች የታገዘ ምርመራ ይሰራል። ህክምናውም ችግሩን እንዳመጣው ምክንያት ይለያያል።
የስንፈተ ወሲብ ህክምና
• በሀኪም ትዕዛዝ በአፍ በሚወሰዱ ክኒኖች እንደ viagra, Levitra, Cialis, Stendra, Slindafil አይነት
• በሆርሞን በመታገዝ
• በብልት ላይ በሚወጋ መርፌ
• በሽንት ትቦ በኩል በሚሰጥ መድሀኒት
• ብልትን የሚወጥር መሳሪያ በመጠቀም
• የብልት ጡንቻ ውስጥ በሚቀመጥ ተመሳሳይ ስሪት
• በቀዶ ጥገና በማስተካከልና በሌሎችም መንገድ ህክምናው ይሰጣል።
2. የአባላዘር በሽታዎች
የአባላዘር በሽታ (STD) ምንድን ነው?
የአባላዘር በሸታዎች ማለት በግብረ ሥጋ ግንኙነት ወይም በጠለቀ አካላዊ ንክኪ የሚተላለፉ በሽታዎች ናቸው ፡፡
የአባላዘር በሽታዎች እንዴት ይተላለፋሉ?
የአባላዘር በሽታዎች የአባላዘር በሽታ ከያዘው ሰው ወደ ጤነኛ ሰው በወሲብ ወቅት ይተላለፋሉ ይህም በአፍ፣በፊንጢጣ እና በሴት ብልት በሚደረግ የግብረ ሥጋ ግንኙነት እና የመራቢያ አካላት የቆዳ ንክኪን ያጠቃልላል፡፡
እንደ ጨብጥ እና ክላማይዲያ የመሳሰሉት በብልት አካል ፈሳሾች የሚተላለፉ ናቸው፡፡ የኤች አይቪ እና ሔፒታይተስ ቢ ቫይረስ ደግሞ በደም ይተላለፋሉ፡፡ ሌሎች የአባላዘር በሽታዎች እንደ ቂጥኝ፣ ጄኒታል ኸርፕስ እና ሂዩማን ፓፒሎማ ቫይረስ የመሳሰሉት ደግሞ በቆዳ ንክኪ የተላላፋሉ፡፡
የአባላዘር በሽታዎች ዝርዝር
✅ ጨብጥ( Syphilis)
✅ ኤች አይ ቪ(HIV)
✅ ቂጥኝ (Gonorrhoea)
✅ ከርክር( Chanchroid)
✅ ባንቡሌ( Inguinal bubo)
✅ ክላሚድያ( Chlamydia)
✅ ትሪኮሞኒያሲስ( Trichomoniasis)
✅ በብልት አካባቢ የሚወጣ ኪንታሮት (Genital warts)
✅ ፓፒሎማ ቫይረስ(HPV)
✅ ዉሃ የቋጠረ የሚያሳክክ ብዛት ያለው የብልት ላይ ቁስል (Genital herpes)
የአባላዘር በሽታ እንዳለብኝ በምን አውቃለሁ?
አብዛኛዎቹ የአባላዘር በሽታዎች ምልክት የማያሳዩ ናቸው፡፡ ስለዚህም በሽታ ሳያስከትሉ ወይም ሳናውቀው ውስጥ ውስጡን እየጎዱን ተዋሲያኑ ሊኖሩብን ይችላሉ ስለሚችል ማረጋገጥ የምንችለው ምርመራ በማድረግ ብቻ ነው፡፡
የአንድ አባላዘር በሽታ መኖር ለሌላ በር ሊከፍት ይችላል:: ለምሳሌ እንደ ኸርፕስ ያሉት የአባላዘር በሽታዎች የኤችአይቪ ቫይረስ እንዲተላለፍ አመቺ መንገድ ስለሚፈጥሩ የራስን እና የፍቅር አጋርን ጤንነት ቅድሚያ በመመርመር መጠበቅ ይቻላል፡፡
• ምልክቶችን ካዩ
• ኤች አይ ቪ ምርመራ
• የቂጥኝ (Syphilis) ምርመራ
• የሄፓታይተስ ቢ ቫይረስ ምርመራ
• የሄፓታይተስ ሲ ቫይረስ ምርመራ
• የፊንጢጣ፣የጨብጥ እና የክላማይዲያ ምርመራ ማድረግ፡፡
የአባላዘር በሽታ ምልክቶች
ምልክቶቹ እንደ አባላዘር በሽታዎች አይነቶች የሚለያይ ሲሆን እንደ አጠቃላይ ግን የሚከተሉት ናቸው፡፡
• ብልት ቆዳ ላይ የሚፈጠር ውሃ ያዘለ ወይም የጎደጎደ ቁስል
• ከሴት ብልት የሚወጣ ፈሳሽ
• ህመም እና ማሳከክ
• የሊምፍ ኖዶች ማበጥ
• በሽንት ግዜ የሚሰማ ህመም
• ከፍተኛ ትኩሳት
• የህመም ስሜት
• የከንፈር መቁሰል
• ቆዳ ላይ የሚፈጠር ውሃ ያዘለ ቁስል
የአባላዘር በሽታን መታከም ይችላል::
አንዳንድ የአባላዘር በሽታዎች እንደ ቂጥኝ፣ ጨብጥ እና ክላማይዲያ ያሉት የአባላዘር በሽታዎች በመድኀኒት የሚድኑ ሲሆን ይህም የሚሆነው የወሲብ ጓደኛችንም ተመርምሮ እና የታዘዘልንን መድኀኒት ጨርሰን ስንወስድ ነው፡፡ ነገር ግን ከዳንን በኋላ ጥንቃቄ የጎደለው ወይም የአባላዘር በሽታ ከያዘው ሰው ጋር የወሲብ ግንኙነት ካደረግን ለአባላዘር በሽታ በድጋሜ ተጋላጭ መሆናችንን መገንዘብ አለብን፡፡
ማሳረጊያ መልዕክት
የግብረ ስጋ ግንኙነት ዘርፈ ብዙ የሆኑ የጤና ጥቅሞችን ይሰጣል:: ነገር ግን ልቅ የሆነ እና ከአንድ በላይ ጓደኛ ጋር የሚደረግ የግብረስጋ ግንኙነት ለአባላዘር በሽታዎች ያለን ተጋላጭነት ይጨምራል:: ስለሆነም ጤናማ የግብረስጋ ግንኙነት ከትዳር አጋርዎት ጋር በማድረግ የጥቅሙ ተቋዳሽ መሆን ይችላሉ::
እንደ አባላዘር በሽታ እና ስንፈተ ወሲብ በአለም ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቁ በሽታዎች ናቸው:: እኚህ በሽታዎች በጊዜ በህክምና ባለሞያ ከታከሙ በሳይንስ የተረጋገጡ መፍትሄዎች አሏቸው:: ስለሆነም እኚህ የጤና እክሎች በሚገጥምዎ ጊዜ ሳይፈሩ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ይታከሙ::
For More Health related Articles Click Here
To Get alerts of our latest Articles Join Our Telegram Channel