March 23 2021
መስፍን ሽመላሽ ፡ ከቀን ሰራተኝነት ተነስቶ የሕክምና ዶክተር የሆነው ወጣት
በሕይወት ዳገት የማይፈተን የለም። ይህን ፈተና ተቋቁመው በፅናት የሚወጡት ግን ጥቂቶች ናቸው። ዶ/ር መስፍን ሽመላሽ ከእነዚህ ብርቱዎች አንዱ ነው።
መስፍን ለቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ ነው። ቤተሰቡ እርሱን ጨምሮ ስምንት ልጆች አሏቸው። ሁለቱ ከአንድ እናት ቀሪዎቹ ደግሞ ከሌላ እናት የተወለዱ ናቸው።
ቤተሰቡ የሚተዳደረው የደርግ ወታደር የነበሩት አባታቸው በሚያመጡት ገቢ ነበር።
አቶ ሽመላሽ በደቡብ ካምፕ ውስጥ በነበሩ ጊዜ በተማሩት የልብስ ስፌት ሙያ ነበር የተሰማሩት። ልባሽ ጨርቆችን በመሸጥም ቤታቸውን ይደጉሙ ነበር።
በዚህ መሃል ግን ታመሙ። ያኔ መስፍን የ4ኛ ክፍል ተማሪ ነበር።
የሙያውን ፈተና ለመጋፈጥ ከከተማ ርቆ የሄደው ሐኪም
ከዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ሳይንቲስቶች መካከል አንዷ የሆኑት ኢትዮጵያዊት
አቶ ሽመላሽ ህመማቸው ከአዕምሮ ጋር የተያያዘ ስለነበር ሥራቸውን መቀጠል አልቻሉም። እርሳቸውን ለማዳን ለስድስት ወራት ያህል መላው ቤተሰብ ተረባረበ። በሕክምና፣ በሃይማኖት፣ በባህልም ተሞከረ፤ አልሆነም። ቤተሰቡ ችግር ላይ ወደቀ።
ሁሉም በየፊናቸው የዘመመ ጎጇቸውን ለማቃናት መታተር ጀመሩ።
ከባለቤታቸው ጋር ተፋትተው ገጠር ይኖሩ የነበሩት የእነ መስፍን እናት ሳይቀሩ ልጆቻቸውን ለማስተማር ወደ ደሴ ተመልሰው በቤት ሰራተኝነት ተቀጠሩ።
ሌሎቹ በሚያውቁት የእጅ ሙያ ተሰማሩ። ታላቅ ወንድሙ ቡታጋዝና ፌርሜሎ [የከሰል ማንደጃ] እየጠጋገነ መሸጥ ጀመረ። አሳዳጊ እናታቸውም አባታቸው የተዉትን የልባሽ ጨርቅ ሥራ ጀመሩ። ግን ከሙያው ጋር እምብዛም ቅርበት አልነበራቸውምና አላዋጣቸውም፤ ከሰሩ።
በዚህ ጊዜ ታላቅ ወንድሞቹ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ። የመጀመሪያው ልጅ ልባሽ ጨርቆችን መነገድ ጀመረ። ሌላኛው ደግሞ ብረታ ብረት ቤት ገባ።
የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ባልጠና ጉልበቱ የብረታ ብረት ሥራ ጀመረ። በዚህ ሁኔታ ወንድሙ ትምህርቱን መቀጠል ባይችልም መስፍን ግን ግማሽ ቀን ጋራዥ እየሰራ፤ ግማሽ ቀኑን ለትምህርቱ ሰጠ።
በእርግጥ እርሱም ቢሆን የሚማረው የማቋረጥ ያህል ነበር። አንድ ወር ቢማር አንድ ወር አይሄድም።
ይህን ገጽ ይዞ ሕይወት ቀጠለ።
ወንድሙ ማታ ማታ ሰርቶ የማይጨርሳቸውን አሮጌ የከሰል ማንደጃዎች እናና ቡታጋዝ ፤ መስፍን በጠዋት ተነስቶ አጠናቅቆ፤ ሸጦ ገንዘቡን ለወንድሙ ሰጥቶ በዚያው ትምህርት ቤት ይሄዳል።
መስፍን በአካባቢው ሰው ቀልጣፋና ጎበዝ እንደሆነ ይታወቃል። በርካቶች ስለእርሱ ወደፊት እምነት ነበራቸው። መስፍን “ጋሽ መሃመድ” እያለ የሚጠራቸው ግለሰብ እጅግ ያበረቱት እንደነበር ያስታውሳል።
“በጋ ላይ የሰራሁትን ወስጄ ስሸጥላቸው ይቆጡኝ ነበር፤ ‘መስራት ያለብህ ክረምት ነው’ እያሉ ትንሽም ቢሆን ገንዘብ ሸጎጥ ያደርጉልኝ ነበር” ይላል።
“አንተ ዶክተር ነው የምትሆነው” ይሉት ነበር።
ምንም እንኳን አብረውት ከሚሰሩት ጓደኞቹ በትምህርት አብረውት የገፉ ባይኖሩም፤ እርሱን ግን በአቅማቸው ይደግፉት ነበር።
ወላጅ እናቱም ሰው ቤት ተቀጥረው በሚያገኙት ገንዘብ ደብተርና የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ አያሳጡትም።
“እናቴ እንደ ህጻን ልጅ “ነይ!” እየተባለች ስትላላክ ማየት ያመኝ ነበር”
መስፍን ተወልዶ ያደገው በደሴ ከተማ እምብርት አራዳ በተባለ አካባቢ ነው።
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመንበረ ፀሐይ፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በንጉስ ሚካኤል እንዲሁም የመሰናዶ ትምህርቱን ሆጤ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
ተምሮ የቤተሰብ ችግሩን መፍታት ምኞቱ ነበር። በሕይወቱ የገጠመውን ፈተና መለወጥ ይፈልግ ነበር።
አባቱ ባጋጠማቸው የአዕምሮ ጤና ችግር ምክንያት፤ ሰዎች “አባቱ እብድ ነው” የሚሉትን ንግግር መቀየር ይፈልግ ነበር።
እናቱንም ለመጠየቅ ሲሄድ ፤ የወለዱት እናቱ እንደ ልጅ “ነይ!” እየተባሉ ሲላላኩ ማየትም ህመም ነበር ለእርሱ። ይህን ለመለወጥ ያለው ብቸኛው አማራጭ ደግሞ ትምህርት ብቻ ነበር።
የሩቅ ህልሙን ለማሳካት ወገቡን አጠበቀ። የአዕምሮ ስንቅም ያዘ።
አባቱ ሌሊት ለፀሎት ሲነሱ ለጥናት ይቀሰቅሱታል። አንብቦ ሲጨርስ፤ አባቱን ፀበል አስጠምቋቸው ወደ አራዳ ይሄድና የሚሸጡ እቃዎችን ዘርግቶላቸው ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ አልፎ በስምንተኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና 99 ነጥብ በማስመዝገብ ወደሚቀጥለው ክፍል ተሸጋገረ።
9ኛ እና10ኛ ክፍልም ቢሆን ከሁሉም ክፍሎች አንደኛ ነበር የሚወጣው። መበለጥን አይወድም።
እርሱ እንደሚለው አስረኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናም ለተማረበት ንጉሥ ሚካኤል ትምህርት ቤት በሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ‘ኤ’ ያስመዘገበው የመጀመሪያው ተማሪ እርሱ ነበር።
ይሁን እንጂ 11ኛ ክፍል በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ላይ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፤ አካሄዱ ወዳለመው የሕክምና ትምህርት ላያስገባኝ ይችላል የሚል ጥርጣሬ አደረበት። 12ኛ ክፍል ላይ አቋርጦ፤ ራሱን በሚገባ አዘጋጅቶ ተፈተነ።
በጊዜው ከፍተኛ የተባለውን 546 ውጤት በማስመዝገብ የሕክምና ትምህርት ለመከታተል ጎንደር ዩንቨርሲቲ ገባ።
ሕይወት በዩንቨርሲቲ፡ “የእናቴ አሰሪ ልጅ አብሮኝ ይማር ነበር”
የሕክምና ትምህርቱ እረፍት የለውም። በርካታ ወጪዎችም አሉት። ይህን ለማሟላት እረፍት ሲኖረው ወደ ቤተሰብ ሄዶ ወደ አሮጌ ቡታጋዝና የከሰል ማንደጃ ጥገና ሥራው ይመለሳል።
ከዚያም ሰርቶ ባጠራቀመው ገንዘብ ለትምህርቱ የሚያስፈልጉትን ያሟላል።
በእርግጥ በዚህ ጊዜ ቤተሰቡ ትንሽም ቢሆን ያግዙት ነበር፤ ነገር ግን ራሱን መርዳት ስለነበረበት ከመስራት ወደ ኋላ አይልም።
ሦስተኛ ዓመት እያለ ግቢ ውስጥ በብረት ብየዳ ሙያ የቀን ሥራ ሰርቷል።
በእርግጥ ፈተናው የኢኮኖሚ ብቻ አልነበረም። የሞራልም እንጂ።
ዩንቨርሲቲ በሁሉም የኢኮኖሚ ደረጃ የሚገኙ ተማሪዎች አንድ ላይ የሚማሩበት ተቋም ነው። አንዳንዱ የቀን ሥራ ሰርቶ ይማራል። በሌላ ጥግ ደግሞ በዘመናዊ ሆቴል እየተመገቡና እየኖሩ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ አሉ።
ይህ በችግር ውስጥ ሆነው ለሚማሩት ሥነ ልቦናዊና ሞራላዊ ተፅዕኖው ቀላል አይደለም። ይህንንም ለመቋቋም ሌላ የመንፈስ ብርታትን ይጠይቃል።
መስፍን “እናቴ አዲስ አበባ ተቀጥራ የምትሰራባቸው አሰሪዎች ልጅ ከእኔ ጋር ሕክምና ይማር ነበር” ይላል። ከአዲስ አበባ ሲመጣም ደረቅ ምግቦችን ይዞለት ይመጣ ነበር።
“ይሰማዋል እያለ ነው መሰል፤ ብዙም አንገናኝም፤ እቃ ሲላክ ሰጥቶኝ ብቻ ነበር የሚሄደው” ይላል።
ዶ/ር መስፍን የሕክምና ትምህርቱን 3.34 በማስመዝገብ በማዕረግ ነው የተመረቀው።
“የተመረቅኩ እለት አባቴ ሲያለቅስ ነው የዋለው፤ ያንን ነገር ሁሉ በማለፌ ደስተኛ ናቸው” ይላል።
የዶ/ር መስፍን ቀጣይ ህልም
ዶ/ር መስፍን በማህፀንና ፅንስ ዘርፍ ሙያውን ማሳደግ ይፈልጋል።
በእርግጥ ከአባቱ የአዕምሮ ጤና ጋር ተያይዞ የአዕምሮ ሕክምና ማጥናት ይፈልግ ነበር። ይህ ሃሳቡ የተቀየረው ለሥራ ልምምድ ከወጣ በኋላ ነው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ያነሳል።
“ከደም ጋር የተያያዘ ሙያ ነው። ውጤቱ ግን እርካታን ይሰጣል። በልምምድ አንድ ዓመት በሰራሁበት ጊዜ ደስ እያለኝ እሰራ ነበር ” ይላል ዶ/ር መስፍን።
ሌላኛው ምክንያቱ ደግሞ በተለይ እንደ ከሚሴ እና አፋር ካሉ አካባቢዎች ወደ ደሴ ከተማ ለሕክምና የሚመጡ እናቶች ስቃይ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች እናቶች በሴት ልጅ ግርዛት የተጠቁ በመሆናቸው በወሊድ ወቅት ይሰቃያሉ። በመሆኑም በሙያው የእነርሱን ስቃይ ለማቅለል በማለም ነው።
“በሽተኛ ሐኪም እየፈለገ፤ ሐኪም ደግሞ ሥራ እየፈለገ መተላለፍ”
ዶ/ር መስፍን ከተመረቀ ወራት ተቆጥረዋል። ውጣ ውረዱን ካለፈለት ሙያው ጋር ግን አልተገናኘም። ሥራ ፍለጋ ላይ ነው።
“ከዚህ ቀደም ጤና ሚኒስቴር ጠቅላላ ሐኪም ይመድብ ነበር። አሁን ግን ‘በጀት የለንም’ ብለው ምደባ አቁመዋል” ይላል ዶ/ር መስፍን።
በእርግጥ በግልም ሥራ ለማግኘት ሞክሯል። ኮምቦልቻ ቤተሰብ መምሪያ ነጻ አገልግሎት ይሰጣል።
ከወንድሞቹ ጋር በመሆን ቤት ለቤት የጤና እንክብካቤ ለመስጠት የሚያስችል ሥራ ለመጀመር እየተንቀሳቀሰ ነው። ይሁን እንጅ ፍቃድ ለማውጣት ቢያንስ ሁለት ዓመት የሥራ ልምድ ያስፈልጋል መባሉን ይናገራል።
“እኛም በተማርንበት ዩኒቨርሲቲ ያ ሁሉ ሐኪም ኖሮ በቀን 30 ታማሚ እናይ ነበር፤ ይህ ሁሉ ታማሚ እያለ፤ ሐኪምን በበጀት ምክንያት መቅጠር አንችልም ማለት ይከብዳል። ያን ሁሉ መከራ አሳልፎም ሥራ ማግኘት አለመቻልም ያማል” ይላል።
“ወደ ጎረቤት አገር ሄዶ መስራት ይቻላል፤ ግን አሁን ባለው ሥርዓት ይህም የማይቻል ነው።” በማለትም አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውን ይገልጻል።
ዶ/ር መስፍን እንደሚለው ጊዜዎች በረዘሙ ቁጥር ሙያውንም መርሳት ይመጣል። ራስን በአዳዲስ እውቀቶች ማበልፀግ የሚቻለውም በሥራ ላይ ‘ኬዝ’ ሲገጥም ነው።
“የቤተሰብ ጉጉት ሲደበዝዝ ማየት፣ ያንን ያህል ዓመት ተለፍቶ፣ የአገር ሐብት ፈስሶ፤ በሽተኛ ሐኪም እየፈለገ፤ ሐኪም ደግሞ ሥራ እየፈለገ መተላለፍ ከባድ ነው” ብሏል
Source :- BBC Amharic