You are currently viewing በሲጋራ ምክንያት እጁን ያጣው ታካሚ‼️

በሲጋራ ምክንያት እጁን ያጣው ታካሚ‼️

February 26 2021

በዶ/ር ሠኢድ መሐመድ (የአጥንት ስፔሻሊስት)
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
በዚህ ሳምንት በምሠራበት የኢትዮጠቢብ ሆስፒታል ካየኋቸው ታካሚዎቼ መካከል እንደተለመደው ሌሎችን ያስተምራል ያልኩትን ገጠመኝ ለአንባቢዎቼ አካፍላለሁ።

አየለ (ስሙ ለዚህ ፅሁፍ ሲባል የተቀየረ) የ 38 ዓመት ጎልማሳ ሲሆን፣ አዲስ አበባ ውስጥ የቀድሞው “አትክልት ተራ” አካባቢ አሁን ሊያሳክመው ባመጣው አንድ ድርጅት ውስጥ ላለፉት ሠባት ዓመታት በወዛደርነት ሲያገለግል ቆይቷል። በግምት ከሁለት ወራት በፊት አየለ የቀኝ እጁ ላይ ህመም ይሠማው ጀመረ። ህመሙ በጊዜው ብዙም ትኩረት ባያገኝም በሂደት እየባሰበት እና እጁም እየደነዘዘ ሄደ። ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን ያስተዋለው አየለ በአቅራቢያው የሚገኝ አንድ ክሊኒክ ታይቶ ማስታገሻ መድኃኒት ብቻ እንደተሠጠው ያስታውሳል።

በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ግን ህመሙ እና ድንዛዜው እየጨመረ፣ ይብስ ብሎ የቆዳውም ከለር እየጠቆረ ሄደ። ሌሎች ተቋማትን እና መንፈሳዊ ህክምናም ሞከረ፣ ለውጥ አልነበረም። በስተመጨረሻ እጁ ሙሉ በሙሉ ጠቁሮ ከታች ያለው ፎቶ ላይ የምትመለከቱት ደረጃ ሲደርስ ወደ ሆስፒታላችን ሪፈር ተደረገ። ምርመራዎችን ሳደርግለት ከክርኑ ከፍ ብሎ ያሉት የደም ስሮች ተዘግተዋል፣ ከክርኑ በታች ያለውም አካል ሞቷል።

ታሪኩን በሚገባ ስጠይቀው እና ተጨማሪ ምርመራዎች ሳደርግ ላለፉት አስር አመታት ያህል ሲጋራ ከማጨሱ ውጪ የደም ስሩን ሊዘጋ የሚችል ሌላ ምክንያት አልነበረውም። የተዘጉት ደምስሮች ሁኔታም አየለ ከሌሎች የደም ስር ህመሞች ይልቅ “ትሮምቦ አንጃይቲስ” በሚሠኘው እና በአመዛኙ በሲጋራ ማጨስ ምክንያት በሚከሠተው እምብዛም ያልተለመደ ህመም ተጠቂ እንደሆነ ያመላክታል። ለመሆኑ ይህ ህመም ምንድነው? መፍትሔውስ? …

 

 

የ”በርገር” በሽታ

አየለ ላይ ያጋጠመው የጋንግሪን (የሠውነት አካል መሞት) ችግር ምንጭ ብዙ ሠዎች ላይ እንደሚያጋጥመን ከልብ ህመም፣ ከስኳር ወይም ከደም ግፊት መዘዝ ጋር የተገናኘ ሳይሆን እምብዛም ያልተለመደ እና የ”በርገር” በሽታ ተብሎ በህክምናው ዓለም የሚጠራ ህመም ነው።

የ”በርገር” በሽታ እኤአ ከ 1879 እስከ 1943 በኖረው ኦስትሪያዊ ሀኪም “ሊዮ በርገር” ስም የተሠየመ የህመም ዓይነት ሲሆን፣ ዶ/ር በርገር በ 1908 ስለ ህመሙ ምንነት የበርካታ ታካሚዎቹን መረጃ በመሠብሰብ የጥናት ውጤቱን ካሳተመ በኋላ የህመሙ መጠሪያ በስሙ ተሰይሟል።

ይህ ህመም “ትሮምቦ አንጃይቲስ ኦብሊተራንስ” በመባልም የሚገለፅ ሲሆን፣ በዚህ ህመም የተጠቁ ሠዎች ላይ የሚኖረው የደም ስር መዘጋት በሌሎች የጋንግሪን መንስኤዎች ከሚኖረው በተለየ መልኩ አነስተኛ እና መካከለኛ ስፋት ያላቸውን የደም ስሮች በማጥቃቱ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት በአመዛኙ ከጉልበት በላይ እና ከክርን መገጣጠሚያ በላይ ያለውን አካል በመተው፣ ከክርን እስከ ጣት፣ ወይም ከቁርጭምጭሚት በታች ያሉ የአካል ክፍሎች ላይ ይበረታል።

አብዛኞቹ የበርገር በሽታ ተጠቂዎች የሲጋራ አጫሾች መሆናቸው በበርካታ ጥናቶች የተረጋገጠ ሲሆን፣ ሲጋራ ማጨሳቸው እንደተለመደው በረጅም ዓመታት የሳምባ ወይም የልብ ህመም በማስከተል በተዘዋዋሪ ደምስራቸው ዘንድ መድረስ ሳያስፈልገው ሂደቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ እና ያለ በቂ “ማስጠንቀቂያ” በቀጥታ የደም ስሮችን የውስጠኛ ክፍል በማጥቃት እንዲዘጉ ያደርጋል። ይህንን ለማረጋገጥ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ፣ በዘር (genetics) የዚህ ህመም ተጋላጭ እንደሆኑ የታወቁ ሠዎች ላይ የሲጋራ ቅንጣቶችን በቀጥታ ወደ ደም ስራቸው በመርፌ በመስጠት ከሌሎች ሠዎች በተለየ ሁኔታ የደም ስሩ የመጥበብ ምላሽ እንደሚሠጥ ታይቷል። ሁኔታው እየባሰ ሲመጣ ልክ እንደ አየለ ሙሉ በሙሉ ጋንግሪን ያመጣና አካሉን በቀዶ ህክምና ማስወገድ የግድ ይሆናል።

የበርገር በሽታን መከላከያ ዋና መንገድ ሲጋራ ማጨስን መቀነስ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ ማቆም ነው። በተለይም ምልክቶች መታየት ከጀመሩ በኋላ በቀን አንድ ሲጋራ ማጨስ እንኳን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ተረጋግጧል። ሲጋራ ማጨስን ከማቆም ባሻገር በሌሎች የደምስር መዘጋት መንስኤዎች ላይ የሚደረጉትን አይነት (መጥበብ የጀመረውን የደም ስር መክፈት የሚያስችሉ) የቀዶ ሕክምናዎች፣ የበርገር በሽታ የሚያጠቃቸው የደም ስሮች ላይ እምብዛም ውጤታማ አይደሉም። ይህም የሆነበት ምክንያት ከፍ ብዬ እንደገለፅኩት ይህ በሽታ የሚያጠቃው በስፋት አነስተኛዎቹን እና “ጨራሽ” (endarteries) የሚባሉትን የደም ስሮች በመሆኑ ነው።

የመድኃኒት ህክምናን በተመለከተ እንደ “አይሎፕሮስት” ያሉ በመርፌ የሚሠጡ መድኃኒቶች በአማራጭነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ እነዚህ መድኃኒቶች በሃገራችን ካለመኖራቸውም በላይ ከአጠራጣሪ ጤታማነታቸው አንፃር ዋጋቸው በጣም ውድ ነው። ስለዚህም ብቸኛው መፍትሔ ሲጋራን አለማጨስ፣ የሚያጨሱ ከሆነ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ማቆም ብቻ ነው። መልካም ጊዜ።

 

Leave a Reply