You are currently viewing “ልጄ እስካሁን ሽንት መቆጣጠር አልጀመረም/አልጀመረችም”- ሽንትን ያለመቆጣጠር ችግር!!

“ልጄ እስካሁን ሽንት መቆጣጠር አልጀመረም/አልጀመረችም”- ሽንትን ያለመቆጣጠር ችግር!!

October 25 2020, ሽንትን ያለመቆጣጠር ችግር

ልጄ ሽንት ይቆጣጠር/ ትቆጣጠር ነበር ከውስን ወራት ጀምሮ መቆጣጠር ተሳናት/ተሳነው ብለው ተጨንቀው የሚመጡ ወላጆች ቁጥር ቀላል አይባልም። እኔም ትንሽ ካነበብኩት ስለዚህ ጉዳይ ጀባ አልኳችሁ::

ሽንትን በተገቢው ዕድሜ መቆጣጠር ያለመቻል ችግር (Enuresis /Bed wetting) ምንነት

👉ልጆች ገና በጨቅላነት ዕድሜያቸዉ ሽንታቸዉ በመጣባቸዉ ሰዓት እንደመሽናት አስደሳች ነገር የሌለ እስከሚመስላቸዉ ድረስ ሽንታቸዉን በመሽናት ራሳቸዉን ሲያዝናኑ ይስተዋላሉ፡፡ ልጆች በህፃንነታቸዉ ወቅት በየትኛውም ሥፍራ ይሁኑ ሽንት ከመጣ “ውረድ እንውረድ ተባባሉና” እንደሚለው አባባል ሽንታቸዉን ማውረድ ብቻ ነዉ የሚታያቸዉ፡፡
ታዲያ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆች ሽንታቸዉን መቋጠርና መያዝ የሚችሉበትን ጊዜ መናፈቃቸው የማይቀር ነው ፡፡ ልጆችንም ሽንታቸዉን እንዲይዙና እንዲቋጥሩ በማብቃት ረገድ የሚቻላቸውን ጥረት ሁሉ ሲያደርጉ ይስተዋላሉ ፡፡ ነገር ግን የተቻለዉን ሁሉ ጥረት ቢያደርጉም አንዳንድ ልጆች ሸንታቸዉን በተገቢዉ ዕድሜ መቆጣጠር ይሳናቸዋል፡፡

ልጄ ሽንቱን መቆጣጠር መቻል ያለበት/ያለባት መቼ ነው?

 

ልጄ ሽንቱን መቆጣጠር መቻል ያለበት መቼ ነው?የሚል ጥያቄ በአንዳንድ ወላጆችና አሳዳጊዎች አዕምሮ ዉስጥ ሊመላለስ ይችላል፡፡ ልጆችንም እርስ በዕርስ በማነፃፀር ችግሩ በአንደኛዉ ስነፍናና ግድየለሽነት የተፈጠረ እስከሚመስል ድረስ ልጆችን ከፍተኛ የሆነ ስነ-ልቦና ጫና ዉስጥ ሲከቷቸዉ ይታያል፡፡
የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው ይባል እንደሚባለዉ ልጆች በሁለንተናዊ (ስሜታዊ፣ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ባሕሪያዊና ማሕበራዊ) ዕድገታቸዉ ለየቅላቸው መሆናቸውን ያሳየናል፡፡ ልጆች ምንም እንኳን በአንድ ማሕፀን ተፀንሰው የተወለዱም ቢሆን በሰሜታዊ፣ አካላዊ፣ አዕምሯዊ፣ ባሕሪያዊና ማሕበራዊ ዕድገታቸው የተለያዩ በመሆናቸው አንድ ልጅ ሽንቱን መቆጣጠር በቻለበት ዕድሜ ሌላኛው ልጅ መቆጣጠር ይችላል ለማለት አያሰደፍርም፡፡
በተጨማሪም አንድ ልጅ ሽንቱንመቆጣጠር የሚችልበትን ቁርጥ ያለውንና እቅጩን የጊዜ ገደብ መናገር እጅግ አዳጋች ነው ይላሉ በመስኩ ያሉ ምሁራን፡፡

በአሜሪካን አገር በተደረገ አንድ ጥናት በ10 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ካሉ 20 ልጆች መካከል አንዱ ልጅ ሽንትን በተገቢዉ ዕድሜ መቆጣጠር ያለመቻል ችግር የተጋለጠ መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ልጆች የሽንት መቆጣጠርና መያዝ ልምምዳቸው እስከ 4 ¨መት ሊቀጥል እንደሚችልና አብዛኛዎቹ ልጆች ለአጭር ጊዜም ቢሆን 5 አመት እስኪሞላቸው ሽንትን ሙሉ ለሙሉ በእንቅልፍ ሰአት መቆጣጠር ያለመቻል ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ታዲያ በዚህን ጊዜ ወላጆችም ሆኑ አሳዳጊዎች መደናገጥም ሆነ መጨነቅ አይኖርባቸውም፡፡ ነገር ግን አንድ ልጅ 6 አመት እና ከዛ በላይ ዕድሜ ክልል ሳለ ሽንትን ለመቆጣጠር ችግር ከገጠመው የባለሙያ ድጋፍ የሚያገኝበትን ሁኔታ ወላጆችም ሆኑ አሳዳጊዎች ማመቻቸት አለባቸው፡፡

ሽንትን መቆጠጠር ያለመቻል ችግር በወላጆች ወይም አሳዳጊዎች ላይ ከሚፈጥረው ስነ-ልቦናዊና ማሕበራዊ ተፅዕኖ ይልቅ በልጆች ላይ የሚፈጥረዉ ተፅዕኖ እጅግ የበረታ ነው፡፡ ልጆች ሆነ ብለው አሰበውና አቅደው ወይም በእነርሱ ግድ የለሽነትና ሥንፍና የሚመጣ ችግር እንዳልሆነ ልንረዳቸው ይገባል፡፡

የሽንት መቆጣጠር ያለመቻል ችግር አይነቶች በዋንኛነት ሁለት ናቸዉ፡፡

 

1ኛ. ከጨቅላነት ዕድሜያቸዉ ጀምሮ ያለማቋረጥ ሽንትን መቆጣጠር አለመቻል እና

2ኛ. አንድ ታዳጊ በትንሹ ለ6 ወራት ያህል ሽንቱን በአግባቡ መቆጣጠር ከቻለ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰት ነው::

ከላይ ለተዘረዘሩት የሽንት መቆጣጠር ያለመቻል ችግር አይነቶች መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉት ዋና ዋናዎቹ እንዲህ ቀርበዋል፡፡

1. በእንቅልፍ ወቅት የሽንት ፊኛ ከመጠን በላይ ሲወጠር መንቃት አለመቻል፡፡
2. በእንቅልፍ ወቅት ሰውነት ብዙ የሽንት መጠን ማምረት፡፡
3. የሽንት ፊኛ ተገቢውን የሽንት መጠን መያዝ ወይም መሸከም አለመቻል፡፡
4. ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት፡፡
5. አስቸጋሪና አሰቃቂ ሁኔታ ውስጥ ማለፍ፡፡
6. ከመጠን በላይ ድንጋጤ እና ፍርሃት፡፡
7. አሰቃቂ አካላዊ ድብደባና ቅጣት፡፡
8. ወሲባዊ ጥቃት/የአስገድዶ መደፈር/ (ለሴት ታዳጊዎች)
9. የአካላዊ ጤንነት ችግር፡፡

ሽንት በተገቢው ዕድሜ መቆጣጠር ያለመቻል ችግር ያሉት ስነ-ልቦናዊና ስነ-ማሕበራዊ ተፅዕኖዎች

 

👉 ለራስ የሚሰጥ ግምትና ዋጋ መወረድ
👉 በራስ መተማመን ማጣት
👉 ጭንቀት ውስጥ መግባት
👉 ለስሜታዊ ጥቃት ተጋላጭ መሆን
👉 በትምህርትና በዕለት ከዕለት በሚኖራቸው የሕይወት እንቅስቃሲያቸው አትኩሮት ማጣት
👉 ራስን የመውቀስና አለመቀበል
ራስን ከቤተሰቡም ሆነ ከማሕበረሰቡ ማግለል

መፍትሄ ይኖረው ይሆን?

 

በእንደዚህ አይነት ችግር ውስጥ ያሉ ታዳጊዎችም ሆኑ ወጣቶችና አዋቂዎች በካውንስሊንግ ሒደት ውስጥ እንዲያልፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ችግሩም ስፋትና ጥልቀት በወራት የሚቆጠር የካዉንስሊንግ ጊዚያቶችን ሊወስድ ይችላል፡፡

አንብበው ሲጨርሱ ለወዳጅ ዘመድዎ ሼር ያድርጉት።

መልካሙን ሁሉ ተመኘሁ

 

Leave a Reply