October 22 2020
ዘንድሮ የጣለው ዝናብ ከፍተኛ መሆኑን ተከትሎ የወባ በሽታ ስርጭት ከባለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ ሊጨምር እንደሚችል የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ይህም ሊሆን የቻለው በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ሳቢያ በርካታ ቦታዎች ላይ ያቆሩ ውሃዎች ይፈጠራሉ ተብሎ ስለሚገመት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በሽታው በተለይ የክረምት ወቅት ማለፉን ተከትሎ ከመስከረም እስከ ህዳር ባሉት ጊዜያት በከፍተኛ ደረጃ ሊስፋፋ ስለሚችል ከወዲሁ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ተብሏል፡፡
በአገሪቱ የወባ በሽታ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስም በአሁን ወቅት የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም በሚኒስቴሩ የብሄራዊ የወባ ፕሮግራም ከፍተኛ ባለሞያ አቶ ደረጀ ዕድሉ በተለይ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ በሽታውን ለመከላከል በቂ የመድኃኒትና የአጎበር አቅርቦት፣ ፈጣን የመመርመሪያ ኪቶችና ማይክሮስኮፕ የማቅረብ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በተለይ 80 በመቶ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍል ጥቅም ላይ የሚውል አጎበር በእጃቸው ያለ ሲሆን የቀሪዎቹ የአገልግሎት ጊዜ ማለፉን ተከትሎ ምትክ አጎበሮችን የማሰራጨት ስራ እየተሰራ እንደሆነም አቶ ደረጀ ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በተመረጡ ቦታዎች ላይ የወባ በሽታ መድኃኒት ከመርጨት ባለፈ ህብረተሰቡን በማስተባበር የወባ ትንኝ መራቢያ አካባቢዎችን ለማጥፋት ውሃ ያቆሩ ቦታዎችንና ዕቃዎችን የማስወገድ የንቅናቄ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በአገሪቱ 75 በመቶ አካባቢዎች ለወባ መራቢያ ምቹ ሲሆኑ በእነዚህ አካባቢዎችም 60 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ የሚኖሩበት እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በ2011 ዓ.ም በበሽታው 900 ሺህ ሰዎች ሲጠቁ በ2012 ዓ.ም ይህ ቁጥር በ40 በመቶ ጭማሪ አሳይቶ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን ተነግሯል፡፡
ህብረተሰቡ በሽታውን ለመከላከል አጎበርን በአግባቡ ከመጠቀም ጀምሮ የተረጩ ቤቶች ግድግዳ ቢያንስ እስከ 6 ወር ምንም ዓይነት ቀለም ሳይቀባ ወይም ሌላ ባዕድ ነገር ሳይለጠፍበት እንዲቆይ ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡
የበሽታው ተጠቂዎች ትኩሳትን ጨምሮ ሌሎች ምልክት ሲታይባቸው በ24 ሰዓት ውስጥ አቅራቢያቸው በሚገኝ ጤና ተቋም ተመርምረው ህክምና ማግኘት እንዳለባቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስገንዝቧል፡፡
#EBC