You are currently viewing 😭 በየሀገሪቱ ጥግ አማራጭ ያጣች ነፍስ አለች!!!😭

😭 በየሀገሪቱ ጥግ አማራጭ ያጣች ነፍስ አለች!!!😭

(አስፋው ክብረት-የተቀናጀ ድንገተኛ የማህፀንና ፅንስ እና አጠቃላይ ቀዶ ህክምና ባለሙያ-IESO)
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።

ማለዳው እሁድ ሆኖ በመስከረም መገባደጃ ላይ ባለ ደመናማ አየር ታጅቧል።ማታ የዘነበው ዝናብ ቀዝቃዛውን ጭጋግና ጭቃውን ትቶ አልፏል።ወደ ንጋት ላይ ኦፕራሲዮን ሰርተን ወጥተን ላባችንን ታጥበን ከቁርስ በሗላ ወደምናዘወትራት የማለዳ ቡናችን ከሆስፒታላችን ወጣ ብለን ታድመናል።

አንድ ባለሞያ ኔትወርክ ስላልነበር እየሮጠ ካለንበት ካፌ ጠርቶን ወደማዋለጃ ክፍል ተያይዘን ሮጥን።ማወለጃ ክፍል ስገባ ጠረኑ ተቀይሯል። የበሰበሰ ስጋ የሚሸተውን አይነት ሸተተኝ። ገና ልጅነቷን በቅጡ ያልጨረሰች ወላድ ከማዋለጃው አልጋ ላይ ተንጋላ በጩኸት ብዛት በተዘጋ ድምፅ እየተወራጨች ታቃስታለች።

ኑሪያ በምጥ ላይ ሶስት ቀናትን አሳልፋለች።በአቅራቢያዋ ጤና ኬላ ብቻ ነበር።እዛም የሔደችው ከሁለተኛው ቀን በኋላ ነበር። ኑሪያ ምጥ በጀመራት በመጀመሪያው ቀን ነበር የህፃኗ እጅ ቀድሞ ከማህፀን የወጣው።ካሁን አሁን ይወለዳል እየተባለ ተጠበቀ ቤተዘመድ ተሰብስቦ መከረ ወጌሻ ይጠራ ተባለ ተጠራ። ሊወጣ የማይችለውን የህፃኑን እጅ በተደጋጋሚ ይስባል። የሕፃኑ እጅ ጋንግሪን እንዳጋጠመው መጥቆር ይጀምራል። አማራጭ ያጣ ዘመድ አዝማድ ለሌላ መፍትሔ መክሮ አቅራቢያ ወዳለ ጤና ኬላ ቢወስዷትም ወደ ሆስፒታል ካልደረሰች እንደምትሞት አበክረው ይነግሯቸዋል። አቅራቢያ ሆስፒታል የለም፣ ያሉበት አካባቢ ኔትወርክም የለም … የትራንስፖርት አገልግሎት አይታሰብም። ሊቀርባቸው የሚችለው ሆስፒታል በሲዳማ የመጨረሻው ወረዳ የሚገኘው ጭሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ነው። እዛ ግን ለመድረስ ቢያንስ ከስምንት ሰዓት በላይ በእግር መጓዝ ነበረባቸው።

ሌሊቱን ሙሉ ወጣቶች ተሰብስበው እየተቀያየሩ ተሸክመው በጥኋቱ 3:00ሰዓት ደረሱ። አሳዛኙ ታሪክ ግን፣ የኦፕራሲዮኑ አልጋ ሊነጋጋ ሲል ሌላ ኦፕራሲዮን ተሠርቶበት ስለነበረ የሚያፀዳው አልነበረም። ደም እንደፈሰሰበት ነው። በብዙ ጭንቅ እኛ ጋ የደረሰችዋ ወላድ ልትወልድ የምትችለው በኦፕራሲዮን ብቻ ነበር። ምንም እንኳ ህፃኗ ሞቶ ቢደርስም አሁን እሷን ለማዳን ነው ርብርቡ። ልጁ በጭንቅላቱ መምጣት ሲገባው በአግድም(transverse lie) ነበር የመጣው። ለማውጣት በማይመች ሁኔታ! …

ፅዳት ሰራተኛ ፍለጋ ሰፈር ለሰፈር የሚፈልግ መልዕክተኛ ተላከ።ኔትወርክ አልነበረም። የነበረን አማራጭ እራሳችን አፅድተን ለኦፕረሲዮን ገባን። ለመግለፅ የሚከብዱ ብዙ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም ፈጣሪ ይመስገን፣ ሕይወቷ ግን ተረፈ። ሰባት ቀን በሆስፒታላችን ቆየች። በመጨረሻም ድና አመስግናን ወጣች።
:
አንዳንዴ በብዙ አቅጣጫ የተበደለ ማህበረሰብ አለ። ኔትወርክ የሌለበት፣ መንገድ የሌለበት፣ ጤና ተቋም የሌለበት፣ … ብዙ የኢትዮጵያ ቦታ አለ። ያሉት ተቋሞቻችንም ዝግጅታቸው አርኪ አይደለም። ቢሆንም በብዙ ቻሌንጅም ቢሆን አንድ አማራጭ ያጣችን ምስኪን ማዳን የህይወት ዘመን ደስታ ነው።

#የታካሚዎቻችን_ታሪኮች

Leave a Reply