October 15 2020
በዶ/ር ሠኢድ መሐመድ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
ክፍል 1
የዛሬዋ ባለታሪካችን የሃያ ስምንት ዓመት ወጣት ናት። በአሁኑ ሠአት ሙሉ በሙሉ ከህመሟ ብትገላገልም፣ ላለፉት ዘጠኝ ወራት ያህል ግን እጅግ ስሜትን በሚረብሽ ተስፋ አስቆራጭ ህመም እየተሠቃየች ቆይታለች። ህመሟ ከሚያሰቃያት ባልተናነሰ ሁኔታ ደግሞ የህመሟን ሁኔታ ለሐኪምም ሆነ ለጠያቂ ለማስረዳት ትቸገር እንደነበረ ትናገራለች። ህክምና ፍለጋ ብዙ ጉልበት ስለባከነችም በወቅቱ ተስፋዋ ተሟጦ ነበር።
መጀመሪያ “ደረቴ አካባቢ ከፍተኛ ህመም ይሠማኛል” ብላ ወደ አንዱ ሀኪም በመሄድ ህክምና እንደጀመረች ታስረዳለች። በወቅቱ የተለያዩ ምርመራዎች ተደርገውላት የሚገኝ ነገር ሲጠፋ እና ህመሙ ከጨጓራ ጋር መመሳሰል ይታይበት ስለነበረ የጨጓራ መድኃኒት ታዘዘላት። መድኃኒቱን በታዘዘችው መሠረት ብትጠቀምም ለውጥ ግን አልነበራትም። ሌላ ሀኪም ዘንድ ሄዳ ሁኔታውን አስረዳች።
እዚያም በድጋሚ ሌላ አይነት የጨጓራ መድኃኒት ስለታዘዘላት፣ ለውጥ አይኖረውም በሚል የታዘዘውን ሳትወስደው ቀረች። ከበርካታ ቀናት ህመም በኋላ ግን ለሳምንታት ያህል ቀስፎ የያዛት የደረት ህመም በራሱ ተሽሏት በቀናት ልዩነት ጀርባዋን ማመም ጀመራት (እንደርሷ ገለፃ “ወደ ጀርባዋ ዞረ”)።
በዚህ መልኩ በተለያዩ የህክምና ተቋማት እየሄደች እና በየደረሠችበት ሲቲ ስካንን ጨምሮ የተለያዩ ምርመራዎችን እያካሄደች ለከፍተኛ ወጪ ብትዳረግም መፍትሔ ባለማግኘቷ እጅግ ግራ ተጋብታ እንደነበረ ታስረዳለች። በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ከጀርባዋ በተጨማሪ ህመሙ እግሯ አካባቢም ይጀምራታል።
ጡንቻዋ እንደበፊቱ ጉልበት እንዳጣም ታስተውላለች። ቀስ እያለ የጀርባዋ ህመም ሙሉ በሙሉ ሲያገግም ደግሞ ትከሻዋን እና የክርኗን ጡንቻ ያማታል። ወዘተ…
በዚህ መልኩ ቦታ እየቀያየረ የሚሠማት ህመም በመቀጠሉ ቢያንስ አምስት የተለያዩ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ጋር እንደታየች እና ህመሟን የሚያውቅላት እንዳላገኘች ታስታውሳለች። እንደ “ሩቃ” ያሉ መንፈሳዊ ህክምናዎችንም ሞክራ ያገኘችው ለውጥ አልነበረም። በተለያዩ የህክምና ተቋማት፣ የምርመራ ውጤቷ “ኖርማል” እንደሆነ የተነገረው ቤተሠቧ “የአዕምሮ ህመም ይኖርባት ይሆን እንዴ?” ብሎ እስከመጠራጠር ስለደረሰ “አመመኝ” ብሎ ማውራቱ ራሱ ያሳፍራት ጀመር።
በእርግጥ ራሷም አዕምሮዋ ልክ ስለመሆኑ የተጠራጠረችበት ወቅት እንደነበረ አልደበቀችኝም። ህመሟ ግን ከአንድ አካሏ ሙሉ በሙሉ በራሱ እያገገመ ወደሌላ አካሏ መሸጋገሩን ቀጥሏል፤ እንደውም እየባሰባት ነው። “አልተሻለሽም?” እያለ የሚያዝን እንጂ መፍትሔ የሚሠጠኝ ባለማግኘቴ “ከሠው ጋር መገናኘት አስጠልቶኝ ነበር” ትላለች። ይህ ደግሞ የመገለል ስሜት እየፈጠረባት ስለነበረ ለረጅም ጊዜ ቢቀጥል ኖሮ ወደ መደበት (Depression) ያልፍና ሌላ የህመም አቅጣጫ ይፈጥር እንደነበረ መገመት ይቻላል።
ከላይ ከጠቀስኳት እንስት ጋር የተገናኘሁት የዛሬ ሁለት ወራት አካባቢ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜዎች በተመሳሳይ ችግር የሚሠቃዩ እንስቶችን አግኝቻለሁ። አብዛኞቹም ልክ እንደርሷ ግራ በመጋባት ከባህላዊውም፣ ከመንፈሳዊውም፣ ከዘመናዊውም ህክምና የተለያዩ ቦታዎችን አንኳኩተዋል። በሚገርም ሁኔታ ከፍተኛ ወጪ አውጥታ ለህክምና ወደ ውጭ ሐገር ደርሳ ያለመፍትሔ የተመለሰችም አጋጥማኛለች።
አብዛኞቹን እንስቶች የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር (በኋላ በማብራራው ምክንያት) አብዛኞቹ አካላቸውን በደንብ የሚሸፍኑ (ጂልባብ፣ ኒቃብ የሚለብሱ) መሆናቸው ቢሆንም፣ አልፎ አልፎ ማንኛውም አይነት አለባበስ የሚለብሱ ፣ የተለያየ ሐይማኖት የሚከተሉ እንስቶች እና በጣት የሚቆጠሩ ወንዶችም አጋጥመውኛል። ህመሙ ግን መኖሩ እስከታወቀ ድረስ አለባበስን መቀየርም ይሁን ማሻሻል ሳያስፈልግ በቀላሉ ሊከላከሉት እና ከተከሰተም በቀላሉ ሊቀረፍ የሚችል ነው።
ከላይ ርዕሴ ላይ በጠቀስኩት ህመም የሚሠቃዩ ሠዎች የህመማቸው ምንነት በቀላሉ እንዳይታወቅ የሚያደርጉትን ምክኒያቶች ለማስተዋል እንደሞከርኩት: አንድም ህመሙ በሀገራችን በምንጠቀምባቸው እና የምዕራቡን ዓለም የበሽታ ስርጭት መሠረት አድርገው በሚፃፉ የህክምና መፅሀፍት ላይ ህመሙ ህፃናት ላይ እንጂ አዋቂዎች ላይ መከሠቱ ያልተለመደ (rare) ተብሎ የሚጠቀስ በመሆኑ እና በሃገራችን ያለው ስርጭት በአግባቡ ያልተጠና በመሆኑ: በዚህም ምክንያት በሕክምና ባለሙያዎች ቀድሞ ስለማይታወስ ይህንን ህመም መሠረት ያደረጉ ምርመራዎችም አለመደረጋቸው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአብዛኛው በህመሙ የሚጠቁ የህብረተሠብ ክፍሎች በመንፈሳዊ ህይወታቸው “ጥሩ” የሚባሉ በመሆናቸው ከህመሙ ልዩ ባህሪም አንፃር ህመማቸውን ከመንፈሳዊ ህመም ጋር በማገናኘት ወደ ህክምና ተቋም አይመጡም፣ አፈትልከው የሚመጡትም ህመማቸው ስለማይገኝላቸው ሌሎች መሠል ህመም ያላቸውን ሠዎች ወደ ህክምና ተቋማት አይጋብዙም።
ይህ “vicious cycle” ሀኪሙን ይበልጥ ከዚህ ህመም ተጠቂዎች እያራቀው እንደአብዛኞቹ የመካከለኛው እና የሩቅ ምስራቅ ህመሞች በአብዛኛው ሐኪም አዕምሮ ከነአካቴው ስለመኖሩ የማይታወስ ሆኗል።
እንዲያውም እንዳስተዋልኩት እንደ ጥቁር አንበሳ እና የካቲት 12 ካሉ ትላልቆቹ የመንግሥት ሪፈራል ሆስፒታሎች ጀምሮ ከተማችን ውስጥ የገዘፈ ስም እስካላቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ላብራቶሪዎች ድረስ የዚህ ህመም ምርመራ አይካሄድም። ለአብነትም ከላይ የጠቀስኳትን እንስት አብዛኛው አንባቢ ያውቀዋል ብዬ ወደምገምተው መንግሥታዊ ያልሆነ ስመጥር ላብራቶሪ ልኬያት “ናሙና ወስደን ወደ ዱባይ እንላክልሽ” እንዳሏት ገልፃልኛለች። ምርመራው እንደልብ የማይገኝበት ምክኒያትም በሃኪሞች በብዛት ስለማይታዘዝ እና ምርመራው በሃገራችን እምብዛም ይፈለጋል ብለው ስለማያስቡ እንደሆነ ገልፀውላታል። በአሁኑ ሠአት አዲስ አበባ ውስጥ እኔ የማውቃቸው ይህን ቀላል የሚባል ነገር ግን እጅግ አስፈላጊ ምርመራ የሚሠሩ ተቋማት በጣም ጥቂት ናቸው።
ፅሁፉ ከዚህ በላይ ቢረዝም አንባቢን ማሠልቸት እንዳይሆን ለዛሬ በዚሁ ይቋጭ። ለመሆኑ ይህንን ህመም በተመለከተ የተሠሩ ጥናቶች ምን ይላሉ? ዓረብ ሐገራት ላይ እና ኢስላማዊ አለባበስ የሚለብሱ እንስቶች ላይ ከሌላው የህብረተሠብ ክፍል ይበልጥ የተለመደ ለምን ሆነ? ህክምናውስ?
ክፍል 2
የአጥንት እና ጡንቻ መልፈስፈስ… (ክፍል ሁለት)
በዶ/ር ሠኢድ መሐመድ
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
በዚህ ርዕስ ዙሪያ በክፍል አንድ ፅሁፌ የአንዲትን ታካሚ ታሪክ ካጋራሁ በኋላ በህመሙ ዙሪያ መሠረታዊ ነጥቦችን ለመዳሰስ በሌላ ክፍል እንደምመለስ ቃል በገባሁት መሠረት ቀሪውን ክፍል እነሆ:—
በቀደመው ክፍል ያወሳናት ታካሚያችን እና በመሠል ህመም የሚሠቃዩ ሠዎች ፣ የችግራቸው ምንጭ የተለያየ ሊሆን ቢችልም አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ግን በሠውነታቸው ውስጥ የሚገኙ እንደ ቫይታሚን እና ኢለመንቶች ያሉ ንጥረ ነገሮች መዛባት ነው። በተለይም የፓራታይሮይድ ሆርሞን መጠን መጨመር ፣ የቫይታሚን ዲ መጠን መቀነስ እና የካልሺየም ስርጭት መዛባት መሠረታዊ ምክኒያቶች ሲሆኑ፣ እነዚህን ለውጦች ተከትሎ ከአጥንት መሳሳት፣ የአጥንት ሽፋን (periosteum) ከዋናው አጥንት ሊቀርብለት ይገባ የነበረውን ድጋፍ (structural support) ማጣት እና ጡንቻ መስነፍ ጀምሮ በተለያዩ የሠውነት ክፍሎች ላይ ለውጦች ይከሰታሉ።
የተለያዩ ጥናቶች እንዳሳዩት እነዚህ ግለሠቦች ከአጥንት እና ጡንቻ ችግሮች ባለፈ በተለያዩ ህመሞች የመጠቃት ዕድላቸው ሠፊ ነው። በተለይም በስኳር ህመም፣ በደም ግፊት፣ በአዕምሮ ህመም፣ በአንጀት / ፕሮስቴት/ ጡት/ ጣፊያ እና የደም ካንሰሮች፣ የመገጣጠሚያ ህመሞች ፣ ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ሊመጡ የሚችሉ ህመሞች ፣ እንደ ቲቢ ያሉ ኢንፌክሽኖችን ጨምሮ በተለያዩ “አውቶ ኢሚዩን” ህመሞች የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ለአብነትም በ2017 ካናዳ ውስጥ የተካሄደ አንድ ጥናት እንዳሳየው ለዚህ ህመም ተጋላጭ የሆኑ ሠዎችን በመለየት 1100 IU ቫይታሚን ዲ እና 1000ሚግ ካልሺየም በየዕለቱ እንዲወስዱ በማድረግ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ሌሎች ህሙማን አንፃር በተለያዩ የካንሠር ህመሞች የመጠቃታቸውን ዕድል እስከ 60% ድረስ ለመቀነስ እንደተቻለ ታይቷል።
ለመሆኑ ለዚህ ህመም የሚያጋልጡ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
ይህ የንጥረ ነገሮች መዛባትን ተከትሎ የሚከሠት ህመም በውስጡ በርካታ ህመሞችን ያቀፈ እንደሆነ አይተናል። ለቫይታሚን ዲ እጥረት እና እርሱን ተከትለው ለሚመጡ ችግሮች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው የሚባሉ የህብረተሠብ ክፍሎች ህፃናት፣ አረጋውያን ፣ የጉበት /ኩላሊት/ አንጀት ህመምተኞች ፣ ከፍተኛ የስብ ክምችት (ውፍረት) ያላቸው ሠዎች፣ ጥቁር ቆዳ ያላቸው ሠዎች ፣ ለረጅም ጊዜ የሚወሠዱ መድኃኒቶችን የሚጠቀሙ ግለሠቦች (ለምሳሌ የሚጥል በሽታ መድኃኒቶች ፣ የአስም መድኃኒት ፣ የፀረ ቲቢ መድኃኒቶች ፣ ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒቶች) ፣ የፀሐይ ብርሀንን በአግባቡ የማያገኙ ሠዎች (ለምሳሌ “ሠን ስክሪን” ቅባቶችን አዘውትረው የሚጠቀሙ፣ ሙሉ አካላቸውን የሚሸፍኑ አልባሳትን የሚያዘወትሩ፣ ከምድር ወገብ ርቀው በሚገኙ ሀገራት ላይ የሚኖሩ ሠዎች፣ በህመም ወይም በሌላ ምክንያት ከቤት የማይወጡ ግለሠቦች፣ ወዘተ…) ይጠቀሳሉ።
ህክምናውስ? …
እነዚህ የህብረተሠብ ክፍሎች ችግሩ እንዳለባቸው በአካላዊም ሆነ የላብራቶሪ ምርመራ ከተረጋገጠ በኋላ እንደሚኖሩበት ቦታ፣ እንደ ዕድሜያቸው እና እንደ አለባቸው የእጥረት መጠን በጠብታ ወይም በእንክብል መልክ በተለያዩ መጠኖች ( 200፣ 400፣ 600፣ 800፣ 1000፣ 2000 ወይም 50,000 IU ) የሚዘጋጁ መድኃኒቶችን እንዲወስዱ ይደረጋል። እጥረቱን ከመቅረፍም በተጨማሪ ለእጥረቱ ያጋለጣቸው ህመም ወይም ሌላ ችግር ተለይቶ ሊታከም ይገባል።
በአለባበስ ምክንያት ተጋላጭ የሚሆኑ ሠዎችን በተመለከተ…
በመጀመሪያው ክፍል ፅሁፌ ላይ እንደጠቀስኩት የቫይታሚን ዲ እጥረትን ተከትሎ የሚመጣው ይህ ህመም ህፃናት ላይ የተለመደ ቢሆንም በተለይ የምግብ ውህድ ጭማሪ (fortification) እና የቫይታሚን ሠፕሊመንት መውሰድ በሚዘወተርበት የምዕራቡ ዓለም አዋቂዎች ላይ የመከሠቱ ዕድል እምብዛም እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ለምድር ወገብ ቅርብ የሆኑ እና አመቱን ሙሉ ፀሐይ የሚያገኙ ሐገራት ላይ ደግሞ ከፍ ብዬ በጠቀስኳቸው በቀላሉ የሚታወቁ ተጓዳኝ ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር በፀሐይ ጨረር እጥረት ምክንያት ይህ ህመም ይከሠታል ተብሎ አይገመትም። ነገር ግን ከኢትዮጵያ በላይ ፀሐይ የሚያገኙ የአረብ ሐገራት ላይ የተሠሩ ጥናቶች፣ በፀሐይ ወቅት ከቤት ያለመውጣት ልማድ በስፋት በመኖሩ ምክንያት እና ሙሉ አካልን የሚሸፍኑ አልባሳት በአካባቢው በመዘውተራቸው ምክንያት ህመሙ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከፍተኛ ስርጭት እንዳለው አሳይተዋል።
በዚህ ዙሪያ በተለያዩ የአረብ ሃገራት ላይ የተሠሩ ጥናቶችን ለማገላበጥ እንደሞከርኩት: በሳኡዲ አረቢያ እስከ 75% ፣ በጆርዳን እስከ 68%፣ እንዲሁም በሊባኖስ ወደ 72% የሚጠጉ ነዋሪዎች የተለያየ መጠን ያለው የቫይታሚን ዲ እጥረት እንዳለባቸው ታይቷል።
በሀገራችን በዚህ ዙሪያ የተደረገ ጥናት ባይኖርም ችግሩ ከሚታሠበው በላይ ሥርጭት እንዳለው እና ጉዳዩ የበርካቶችን ቤት እንዳንኳኳ ማስተዋል ይቻላል። ጉዳዩ በአብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች ስለማይጠረጠር ግን እምብዛም መኖሩ አይታወስም፣ ተገቢው ምርመራም ይሁን ህክምና በስፋት ሲደረግ አይታይም።
መፍትሔውስ?
በቂ የፀሐይ ጨረር ወደ ቆዳ ባለመድረሱ ምክንያት የሚመጣውን የቫይታሚን ዲ እጥረት ለመከላከል ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እና በተለይም ሙሉ አካላቸውን የሚሸፍኑ ወይም በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት የማይወጡ ሠዎች ሆነ ብለው ፕሮግራም በማውጣት ቢያንስ በሳምንት ለአራት ቀናት፣ ከአስር እስከ ሰላሳ ደቂቃዎች ያህል ቆዳቸውን ለቀጥተኛ የፀሐይ ጨረር የሚያጋልጡበትን ሁኔታ ማመቻቸት አለባቸው። ይህ ካልተቻለ ደግሞ እንደ ዕድሜያቸው በተለያዩ መጠኖች የሚዘጋጁ እንክብሎችን (supplements) በየዕለቱ በመውሠድ ሊያጋጥም የሚችለውን እጥረት በቀላሉ መከላከል ይቻላል። እንደ አሳ ያሉ ምግቦችን ማዘውተርም በዚህ ረገድ ይመከራል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በቀደመው ፅሁፌ ላይ ከጠቀስኳቸው የህመም ስሜቶች ውስጥ የተወሰኑት ወይም በሙሉ ከተከሠቱ ደግሞ: ህመሙ ከመስፋቱ እና ካንሰርን ጨምሮ ከላይ የተዘረዘሩት መጠነ ሠፊ ጉዳቶች ከመድረሳቸው በፊት ወደ ተገቢው የህክምና ተቋም በመሄድ መታከም ይኖርባቸዋል።
It is amazing literature but Where can i get the laboratory for this disease in Addis Ababa …thank you