You are currently viewing የሀኪሙ ገጠመኝ ፣ ለልጇ ብላ የሞት አፋፍ ላይ ያለችው እናት‼️

የሀኪሙ ገጠመኝ ፣ ለልጇ ብላ የሞት አፋፍ ላይ ያለችው እናት‼️

October 12 2020

ዶ/ር ሸምሠዲን ሙሠፋ (የነርቭ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት )
።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።።
የዛሬዋ ባለታሪክ አሠለፈች ትባላለች (ስሟ ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ተቀይሯል)። ዕድሜዋ ሠላሳ ስድስት ዓመት ሲሆን የሶስት ልጆች እናት ናት። እንደ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ኑሮዋ “ከእጅ ወዳፍ” ሲሆን ከባለቤቷ እና ከልጆቿ ጋር አዲስ አበባ ውስጥ ትኖራለች። ይህ ነው የሚባል ከባድ ምክንያት ባይኖርም አልፎ አልፎ ከባለቤቷ ጋር በቀላሉ ከረር ያለ ፀብ ውስጥ እየገቡ መልሠው ይታረቃሉ። እንዲያውም ከጥቂት ዓመታት በፊት እንደተለመደው በቀላል ነገር ተጋጭተው ድብደባ ስለፈፀመባት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሎ እንደነበረ እና ከእስር ሲለቀቅ መልሠው አብረው መኖር እንደቀጠሉም አስታማሚዋ ትናገራለች።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ወደ ሆስፒታላችን ስትመጣ በሞት እና በህይወት መሃል ነበረች። ጭንቅላቷ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይደማል፣ የቀኝ እጇም እንደዚያው። በእለቱ ከፍተኛ ርብርብ አድርገን፣ ፈጣሪም ረድቶን ህይወቷን ለማትረፍ ብንችልም፣ ጉዳቱ ከፍተኛ ስለነበረ ከዚያ በኋላ በነበሩት ቀናትም የነበራት ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነበር። የጭንቅላቷ አጥንት በርካታ ቦታዎች ላይ ከመሠባበሩም በላይ የተወሠኑ ቦታዎች ላይ ከነአካቴው የቀረ አጥንት ስላልነበረ የተወሠነ የአንጎሏ ክፍል ያለአጥንት ሽፋን ቀርቷል። በጥቅሉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት (እስከትላንትና ድረስ) አምስት ጊዜ የጭንቅላት ቀዶ ህክምና አድርገንላታል። ከዚህም በኋላ ብዙ ልፋት የሚጠበቅብን ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ግን ቢያንስ ያለ ኦክስጂን መተንፈስ እና ማውራት ችላለች። ያጋጠማትንም በራሷ አንደበት እንደሚከተለው ተረከችልን …

“ባለቤቴ በቀላሉ የሚቆጣ ‘ግልፍተኛ‘ ነገር ነው። በውሃ ቀጠነ ካልደበደብኩሽ እያለ አንዳንዴ በጎረቤት ጣልቃ ገብነት፣ አንዳንዴ ደግሞ ደብድቦኝ ሲወጣለት እየተወኝ ነው የኖርነው። ልጆቹንም በትንሽ በትልቁ ይቆጣቸዋል፣ ሲያሰኘውም ይደበድባቸዋል። ኑሮዬ እንዳይበተን ፣ ልጆቼንም የማጎርሠው እንዳላጣ ስል ሁሉንም ችዬ ኖሬያለሁ። በዚያ ሠሞን ትልቁ ልጄ ከጓደኞቹ ጋር ሲጫወት ቆይቶ ሲመለስ ሳልፈቅድልህ እንዴት ከቤት ትወጣለህ ብሎ እስኪበቃው ገረፈው። ከዚህ በኋላ ከቤት ወጥቶ ቢመለስ እንዳላስገባው አስጠነቀቀኝ።

ከጥቂት ቀናት በፊት የልጅ ነገር ሆኖ ከጓደኞቹ ጋር ለመጫወት ሳናየው ወጣ ብሎ ሲመለስ አባቱ ካወቀ አይለቀውም ብዬ፣ ሁለተኛ እንዳይለምደው ተቆጥቼው ቶሎ እንዲገባ አደረግኩ። ባለቤቴ ለካ ይህንን ተመልክቶ ነበረና ከጓሮ ወፍራም የፌሮ ብረት ይዞ መጥቶ ያለርህራሄ ጭንቅላቴን እንደ እባብ ቀጠቀጠኝ። ራሴን በሳትኩበትም እስኪደክመው ከመታኝ በኋላ ሞታለች ብሎ ትቶኝ እንደሄደ ሠምቻለሁ። ጎረቤቶቼ የልጆቼን ጩኸት ሠምተው አንስተውኝ ወደዚህ አመጡኝ። የወደፊቱን ባላውቅም ዕድሜ ለእናንተ ህይወቴ ተረፈች። እርሱ ግን በፖሊስ የተያዘም አይመስለኝም፣ አሁንም ለልጆቼ እሠጋለሁ … ይኸው ነው።”

ታካሚያችን ሙሉ በሙሉ ድና እስክትወጣ ጥረታችንን እንቀጥላለን። አንድ ግለሠብ ግን በውሃ ቀጠነ የቤተሠቡ አባል፣ ያውም የልጆቹ እናት ላይ እንዴት እስከዚህ ድረስ ሊጨክን ይችላል? ይህን መሠሉ ወንጀልስ ማቆሚያው የት ይሆን??

 

Leave a Reply