October 12 2020
በዶ/ር ዮናስ ላቀው
መንደርደሪያ
ህክምና ስንማር አንድ ዝምተኛ የክፍላችን ልጅ ነበር። ክፍል ልክ ሊጀመር ሲል ድምፅ ሳያሰማ ከኋላ ገብቶ ይቀመጣል።ትምህርት ሲያልቅ ቶሎ ይወጣና ካፌ በልቶ ወደ ‘ቴንሽን ቦክሱ’። ከሰው ጋር አይቀላቀልም። በጣም ጎበዝ ነው። የፅሁፍ ፈተናዎቹን ከፍተኛ ውጤት ያመጣና የቃል ፈተና (Oral exam) ሲሆን ግን ጭንቅ ጭንቅ ይለዋል። የሚያውቀው ይጠፋበታል። ሲመልስም ድምፁ ይንቀጠቀጣል።
አንድ ፈታኝ “ስጠይቅህ አትመልስም፤ የፅሁፍ ውጤትህ ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው። ኮርጀህ ነው እንዴ?” ብሎታል።’ፕረዘንተሽን’ ወይም የቡድን ስራ ሲኖር ምቾት ስለማይሰማው ጥሎ ይሄዳል።
እስከ ሶስተኛ አመት እንደምንም እንደምንም ቀጠለ። ሆስፒታል መሄድ ስንጀምር ታካሚን መመርመር፣ የቃል ትምህርት፣ ብዙ ‘ፕረዘንቴሽን’ ማቅረብ ስለነበረብን ይህንን መቋቋም አቅቶት ትምህርቱን ትቶ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። በእውቀት ከአብዛኞቻችን የተሻለ የነበረው ልጅ ትምህርቱን ያቋረጠው በማህበራዊ ፍርሀት (Social phobia) ምክኒያት ይሆንን የሚለው ጥያቄ አልፎ አልፎ ድቅን ሲልብኝ ይደርስ የነበረበትን አስቤ አዝናለሁ።
በማህበራዊ ፍርሀት (Social phobia) ምክኒያት ብዙዎች ከሚገባቸው ያነሰ ውጤት ተሰጥቷቸዋል። ብዙዎች ጥሩ ውጤት እያላቸው የስራ ቃለመጠይቅ ላይ በደንብ መናገር ስላልቻሉ ስራ ሳያገኙ ቀርተዋል። ብዙዎች ስራቸው ላይ ጎበዝ ሆነው ስብሰባና ‘ፕረዘንቴሽን’ ስለሚጨንቃቸው የሚገባቸው ደረጃ ላይ አልደረሱም።
ማህበራዊ ፍርሀት (Social phobia) ውጤታማ ህክምና አለው።
ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ሌሎች ሰዎች ባሉበት ዘና ማለት አይችሉም፡፡ ሌሎች ሰዎች የእነሱን ንግግር ወይም ድርጊት የሚገመግሙና የሚተቹ ስለሚመስላቸው ይፈራሉ፡፡ስህተት እንዳይሰሩና እንዳይዋረዱ ስለሚፈሩ ዘና ብለው እንደሚፈልጉት ከሰዎች ጋር መጫወት ይከብዳቸዋል ፡፡
አብዛኛው ሰው ካልለመደው ሰው ጋር ሲሆን የአለመመቸት ስሜት ይፈጠርበታል፡፡ ሶሻል ፍቢያ ሲሆን ግን ፍርሀቱ በጣም የበዛ ይሆናል፡፡ ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች አብሯቸው ያሉ ሰዎች ሲጫወቱ ፣ሲስቁ ፣ሲያወሩ እነሱ መሣተፍ ስለማይችሉ ብቸኝነት ይሰማቸዋል፡፡
ብቻቸውን ግን አይደሉም፡፡ ከአስር ሰው አንዱ ተመሣሣይ ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ ነገ መንገድ ላይ ሲሄዱ አስር ሰዎች ይቁጠሩ ከዛ ውስጥ አንዱ ሶሻል ፍቢያ አለበት/አለባት፡፡
የሶሻል ፎቢያ ምልክቶች በጥቅቱ፦
-ከቤት ውጪ ምግብ ባይበሉ ይመርጣሉ፡፡ለብቻቸው ሬስቶራንት ገብተው፣ ባዶ ጠረጴዛ ፈልገው፣ ‘ያ ሁሉ ሰው’ እያያቸው መመገብ ይከብዳቸዋል፡፡
-ዝግጅቶች ላይ በግድ ነው የሚገኙት (እሱንም ከተገኙ!)-እስከቻሉት ድረስ ምክኒያት ፈጥረው ለመቅረት ይሞክራሉ፡፡
-በአብዛኛው የድካም ስሜት ይሰማቸዋል፡፡
-ሰዎች ሲሰበሰቡ ከመጨነቅ ጋር ተያይዞ ልብ ቶሎ ቶሎ መምታት፣ ትንፋሽ ቁርጥ-ቁርጥ ማለት፣ ማላብ
– ነገሮች እጅግ አስከፊ ሊሆኑ እንደሚችሉ በማሰብ መጨናነቅ ፣እንቅልፍ ማጣት
– የፍቅር ቀጠሮች ላይ (በተለይ የመጀመሪያዎቹ ላይ) ምን እንደሚባል አለማወቅ…
ከላይ የተዘረዘሩትን ሶሻል ፎቢያ ያለባቸው ሰዎች ይረዱታል፡፡ ሌሎች ግን ቀለል አድርገው ሊያዩት ይችላሉ፡፡ ሶሻል ፎቢያ ተማሪዎች እውቀት እያላቸው ጥሩ ውጤት እንዳይኖራቸው፤ ሰራተኞች ችሎታ እያላቸው የሚገባቸውን እድገት እንዳያገኙ፣ እንዲሁም ለሚወዱት ሰው ፍቅራቸውን መግለፅ እንዳይችሉ ያደረጋል፡፡
ሶሻል ፎቢያን ማሸነፍ ይቻላል ነገር ግን ትዕግስትና ቁርጥኝነት ይጠይቃል፡፡
በራሳችን ልናደረግ የምንችለው
1. ሀሣብን መገምገም፦ በሶሻል ፎቢያ የሚቸገሩ ሰዎች ጭንቀትን የሚያባብሱ ሀሳቦች አላቸው፡፡
ለምሳሌ ፡- ፡”እንደ ሞኝ መቆጠሬ አይቀርም፡፡” “መናገር ስጀምር ድምፄ ይንቀጠቀጥና ራሴን አዋርዳለሁ፡፡ ” “አንደፈራሁ ሰዎች ያውቁብኛል፡፡” እነዚህን ሀሣቦች መገመገምና መሞገት ጭንቀቱን ይቀንሣል፡፡
2. ከሰዎች ጋር ሲሰበሰቡ ሌሎች ላይ ማተኮር፤ በራስ ጭንቀት ከመጠመድና ፍርሃትን ስለመሸፈን ከመጨነቅ ሌሎች ሰዎች የሚያደርጉትና የሚናገሩት ነገር ላይ ማተኮር ጭንቀትን ይቀንሳል ፡፡ ሰዎች በአብዘኛው የሚያስቡት ስለራሳቸው ስለሆነ የሚገምተውን ያህል መፍራታችንም አያውቁም፡፡
3. አተነፋፈስን ማስተካከል – በፍርሃት ጊዜ በአብዛኛው ከላይ-ከላይና ቶሎ-ቶሎ ነው የሚተነፈሰው ፡፡ ይህ ጭንቀትን ያባብሳል ፡፡- በቀስታ በጥልቀት መተንፈስ ረጋ ያለ ስሜትን ይፈጥራል ፡፡
4. አነቃቂ ነገሮች የጭንቀት ስሜትን ስለሚያባብሱ እነሱን መቀነስ፡፡
እነዚህ ተደረገው አሁንም ስሜቱ ካለ የህክምና እርዳታ ያስፈልገዋል፡፡
መልካም ጊዜ!