You are currently viewing ኮቪድ-19 ከእያንዳንዱ ሁለት ታማሚ መካከል የአንዱን አእምሮአዊ ጤና አቃውሷል‼️

ኮቪድ-19 ከእያንዳንዱ ሁለት ታማሚ መካከል የአንዱን አእምሮአዊ ጤና አቃውሷል‼️

  • Post author:
  • Post category:News
  • Post comments:0 Comments

October 10 2020

ኮቪድ-19 የአእምሮ ጤና ሁኔታን የበለጠ አባብሷል። በሰባት አገራት ውስጥ ከሁለት ሰዎች መካከል አንድ ሰው ላይ የአእምሮ ጤና ችግር ማስከተሉን ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ይፋ ያደረገው ጥናት አመልክቷል።

በየዓመቱ መስከረም 30 ላይ ከሚከበረው የዓለም የአእምሮ ጤና ቀን ከመከበሩ አስቀድሞ ይፋ የተደረገው ጥናት፣ በኮቪድ-19 ወቅት የአእምሮ ጤና እና የሥነማኅበራዊ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ለማሳየት ያለመ ነው ተብሏል።

በመሆኑም በመላው ዓለም የሚገኙ መንግሥታት እና ማኅበረሰብ አቀፍ ድርጅቶች አስፈላጊ ለሆኑ ፍላጎቶች ምላሽ ሊሰጡ እንደሚገባ አሳስቧል።

በጥናቱ ላይ የተሳተፉ 75 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች በግንባር ላይ የተሰለፉ የጤና ባለሞያዎች በአእምሮ ጤና የከፋ ተጠቂዎች መሆናቸውን እንደሚያምኑ እና ከመደበኛ ሰው የበለጠ የጤና ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል።

67 በመቶ የጤና ተሳታፊዎች ደግሞ አእምሮአዊ እና አካላዊ ጤና መጠበቅ ከኮቪድ-19 በፊት ከነበረው የበለጠ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሜቴ ዋና ዳይሬክተር ሮበርት ማርዲኒ፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሣ የተከሰቱት የእንቅስቃሴ እቀባዎች፣ የማኅበራዊ ትስስስር መቆም፣ ሥራ አጥነት እና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎች በሰዎች አእምሮአዊ ጤና እና ሕክምና ማግኘት ላይ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል። ግጭቶች እና አደጋዎች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደግሞ ስር የሰደደ ሥነ ልቦናዊ ጫና ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ እና የዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ የአእምሮ ጤና ቀንን አስመልክቶ ባወጡት መረጃ ለሁሉም ተደራሽ መሆን የሚችል የአእምሮ ጤና ክብባካቤ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ለዚህም በምክንያትነት እጅግ ጥቂት የሆኑ የአእምሮ ታማሚዎች ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ማግኘታቸውንና ባለፉት ዓመታት አገራት ከጤና በጀታቸው ውስጥ ሁለት በመቶ ብቻ ለአእምሮ ሕክምና ማዋላቸውን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ወደ አንድ ቢሊየን ገደማ የሚሆኑ ሰዎች ከአእምሮዊ ጤና ቀውስ ጋር እንደሚኖሩ፣ ሦስት ሚሊየን የሚሆኑት ጎጂ በሆነ የአልኮል አጠቃቀም በየዓመቱ እንደሚሞቱ፣ በእያንዳንዱ 40 ደቂቃ አንድ ሰው ራሱን እንደሚያጠፋ እና አብዛኞቹም በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት ውስጥ የሚገኙ መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት አሐዛዊ መረጃ እንደሚያሳይ የሲጂቲኤን ዘገባ ያመለክታል።

 

 

Leave a Reply