You are currently viewing ማይክሮሶፍት ሠራተኞቹ ከኮቪድ-19 በኋላም ከቤታቸው እንዲሰሩ ፈቀደ!!

ማይክሮሶፍት ሠራተኞቹ ከኮቪድ-19 በኋላም ከቤታቸው እንዲሰሩ ፈቀደ!!

October 10 2020

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከቤት መሥራትን አስገዳጅ አድርጎታል፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ግን ግዙፉ ማይክሮሶፍት ለሠራተኞቹ ትልቅ የብሥራት ዜና ይዞ መጥቷል፡፡ ካንፓኒው ለሰራተኞቹ ወረርሽኙ ሲጠፋም ግን ከቤት ሆናችሁ መሥራት መብታችሁ ነው ብሏቸዋል፡፡
ይህም ወደ ፊት ለሥራ ወደ ቢሮ መምጣት የግድ እንደማይሆን ያመላከተ ውሳኔ ሆኗል፡፡
የማይክሮሶፍት ሠራተኞች በቋሚነት ከቤት፣ ከካፌ ወይም ከፈለጉበት ሆነው ሥራቸውን መከወን እንዲችሉ በቅድምያ የሥራ አስኪያጃቸውን ይሁንታ ብቻ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከማይክሮሶፍት በፊት ሌሎቹ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ተመሳሳይ ሐሳብ አንስተው ነበር፡፡ በተለይም የፌስቡክና የትዊተር ሠራተኞች ወደፊት ከቤት ሆነው ሥራቸውን ማሳለጥ እንደሚችሉ ተስፋ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በርካታ ግዙፍ የዓለማችን ኩባንያዎች ይህንን የቤት አሠራር ከግምት በማስገባት ላይ ናቸው፡፡ ነገሩን በጥሞና እያሰቡበት እንደሆነ አመላካች የሆነው የቢሮ ይዞታቸውን ለመቀነስ እየሰሩ መሆኑ ነው፡፡
ማይክሮሶፍት እንደሚለው አንዳንድ የሥራ መደቦች በባህሪያቸው ቢሮ መገኘትን የግድ የሚሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን አብዛኛዎቹ ሠራተኞቹ የግድ ቢሮ መምጣት የለባቸውም፡፡
ከፈለጉበት ሆነው ሥራቸውን እስከሰሩ ድረስ ኩባንያው ደስተኛ ይሆናል ብለዋል፡፡
የማይክሮሶፍት ቃል አቀባይ ‹የኛ ህልም ከጊዜ ጋር መራመድ፣ ጊዜው የሚፈልገውን ማቅረብና ለሠራተኞቻችን ምቹ መሆኑ ነው፡፡ ከቤት የመሥራቱ ሐሳብም የዚህ አካል ነው›› ብለዋል፡፡
በርካታ ሠራተኞች ኮሮናቫይረስን ተከትሎ ከቤት መሥራት ውጤታማና ምርታማ አድርጎናል ሲሉ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ጊዜው በሄደ ቁጥር ይህ ሐሳባቸው እየተቀየረ መምጣቱ ነው የተነገረው፡፡
የማይክሮሶፈት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ትውልደ ህንዳዊው ሳቲያ ናዴላ ሰሞኑን በነበረ አንድ ስብሰባ ላይ እንዳሉት፤ በግል ሕይወታችንና በሥራችን መሀል መስመር ስናጣ ሥራ ላይ እያንቀላፋን እንዳለን ያህል ነው የሚሰማን ብለዋል፡፡
ብዙ ኩባንያዎች ከኮሮናቫይረስ በኋላ የሥራ አካሄድ ምን ሊመስል ይችላል በሚል ውይይት ጀምረዋል፡፡
የአብዛኛዎቹ ምርጫ ግን በሳምንት ቢያንስ ሁለት ቀናት ሠራተኞች ከቤት ሆነው መሥራት እንዲችሉ ማመቻቸት ነው፡፡
የተቀሩት ቀናት ግን ሠራተኞች ከአለቆቻቸው ጋር በአካል እየተገናኙ ቢወያዩ የሥራ መንፈስን ማጎልበት ይቻላል፣ ለመሥርያ ቤቱ ታማኝ መሆንን ያረጋግጣል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለአእምሮ ጤናም መልካም ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ ከቤት መሥራት በረዥም ጊዜ ሂደት ለጤና እክልና ለመሰላቸት ሊዳርግ ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
በአንጻሩ ግዙፍ ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸው ከቤት እንዲሰሩ ሲፈቅዱ በከተሞች አካባቢ የቢሮ ኪራይ ፍላጎት እየቀነሰ እንዳይመጣ ተሰግቷል፡፡
በዋና ከተሞች አካባቢ ቤት ኪራይ የመወደዱ አንዱ ሚስጢርም ለቤት ቅርብ ሆኖ ከመስራት ጋር የተያያዘ ነው፡፡
በኒውዮርክና ሳንፍራንሲስኮ ይህ ከወዲሁ እየታየ ነው፡፡ በሁለቱ ከተሞች የቢሮና የቤት ዋጋ ኪራይ መጠነኛ ቅናሽ አሳይተዋል፡፡

Leave a Reply