September 30 2020
የዓለም ባንክ ለታዳጊ አገራት ለኮቪድ-19 ክትባት የሚውል 12 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ የባንኩን ቦርድ ውሳኔ እየተጠባበቀ ነው::
የዓለም ባንክ ለታዳጊ አገራት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19 ) ክትባትን ለማምረትና ለማሰራጨት የሚውል 12 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ የባንኩን ቦርድ ውሳኔ እየተጠባበቀ መሆኑን የባንኩ ፕሬዝዳንት ዳቪድ ማልፓስ ተናገሩ፡፡
ባንኩ ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋባቸው በሚገኙ በደሃና በአዳጊ ሀገራት ክትባቱን ተደራሽ ለማድረግ ያለውን የአቅም ችግር ለማሟላት ዓላማ እንዳለው ነው ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡
ዋና ዓላማችን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት የወረርሽኙን አቅጣጫ መቀየር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ የባንኩ ቦርድም በሚቀጥለው ጥቅምት ወር ውስጥ በጉዳይ ዙሪያ አንድ ውሳኔ እንሚያሳልፍ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የኮቪድ-19 ክትባት ፍላጎት ከፍተኛ መሆን ለክትባት አምራች ድርጅቶችም የማምረት ስራ እንዲጀምሩ ያነሳሳል ተብሏል፡፡
የኮቪድ-19 ክትባት ለገበያ ሲቀርብ በታዳጊ ሀገራት የክትባቱን ተደራሽነት ከፍ ለማድረግ ዓለም አቀፍ አጋር አካላት የ160 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸው ይታወሳል ሲል የዘገበው ሮይተርስ ነው፡፡
#Reuters
#EBC