You are currently viewing 🎥 የዓለም ጤና ድርጅት 120 ሚሊዮን ፈጣን የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪቶችን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት ሊያቀርብ ነው‼️

🎥 የዓለም ጤና ድርጅት 120 ሚሊዮን ፈጣን የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪቶችን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው አገራት ሊያቀርብ ነው‼️

  • Post author:
  • Post category:News
  • Post comments:0 Comments

September 29 2020

 

ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ላላቸው ሀገሮች 120 ሚሊዮን ጥራት ያላቸው ፈጣን የኮቪድ-19 መመርመሪያ ኪቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ከስምምነት መደረሱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

አዲሶቹ መመርመሪያዎች የኮቪድ-19 ውጤትን ከ15-30 ደቂቃ ውስጥ ማወቅ እንደሚያስችሉ ተገልጿል።

ኮቪድ-19ን በደቂቃዎች ውስጥ የሚለይ ምርመራ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመለየት ሥራን እንደሚያሳድግ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

አምስት ዶላር ብቻ የሚያስወጣው ይህ ምርመራ የጤና ባለሙያዎች እና የላብራቶሪ እጥረት ባለባቸው ድሃ ሀገራት የኮቪድ-19 ሕሙማንን ለመለየት በእጅጉ እንደሚረዳ ነው የተገለጸው።

መመርመሪያውን ከሚያመርቱ ድርጅቶች ጋር የተደረገ ስምምነት በስድስት ወር ውስጥ 120 ሚሊዮን መመርመሪያዎችን ለማምረት ያስችላል።

እንደ ቢቢሲ ዘገባ፣ በበርካታ አገራት ምርመራ ከተደረገ በኋላ ውጤት ለማወቅ የሚፈጀው ጊዜ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያርጉትን ትግል ጎድቶት ቆይቷል።

ይህ አዲሱ “ተንቀሳቃሽ እና ለአጠቃቀም ምቹ የሆነ” መመርመሪያ ውጤትን ከ15 እስከ 30 ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሚሰጥ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ሰኞ ዕለት በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ግን የኮሮናቫይረስን ውጤት ለማወቅ ሰዓታት ካልሆነም ቀናት እንደሚፈጅ ይታወቃል።

አቦት እና ኤስዲ ባዮሴንሰር የተባሉ መድኃኒት አምራቾች ከቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን 120 ሚሊዮን መመርመሪያዎችን ለማምረት ስምምነት መድረሳቸውን ዶ/ር ቴድሮስ ጨምረው ገልጸዋል።

በዚህ ስምምነት መሠረት የሚመረቱ መመርመሪያዎች በቫይረሱ በጣም የተጎዱ የላቲን አሜሪካ ሀገራትን ጨምሮ ለ133 ሀገራት ይሰጣል ተብሏል።

“ይህ በተለይ ከፍተኛ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የመመርመር አቅም ላይ ትልቅ እመርታ የሚፈጥር ነው” ብለዋል ዶ/ር ቴድሮስ።

“ላቦራቶሪ በሌላቸው እና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ወይንም ምርመራውን ለማካሄድ በቂ የሰለጠነ ባለሙያ በሌለበት አካባቢ የመመርመር አቅምን ያሰፋል።” ሲሉም አክለዋል።

 

Leave a Reply