You are currently viewing በኢትዮጵያ በአስከሬን ላይ የሚደረገው የኮቪድ-19 ምርመራ መቆሙ ተገለፀ‼️

በኢትዮጵያ በአስከሬን ላይ የሚደረገው የኮቪድ-19 ምርመራ መቆሙ ተገለፀ‼️

  • Post author:
  • Post category:News
  • Post comments:0 Comments

September 29 2020

ኢትዮጵያ ከአስከሬን ላይ ናሙና በመውሰድ ታደርገውን የነበረውን የኮሮናቫይረስ ምርመራ ማቆሟን አስታውቃለች።

ይህንን ያስታወቀውም የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ በፃፈው ደብዳቤ ነው።

የአለም ስጋት ሆኖ የቀጠለውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት አገሪቷ የተለያዩ የመካላከልና የመቆጣጠር ስራዎችን እየሰራች እንደነበር የጠቀሰው ደብዳቤው ከነዚህም መካከል ከአስከሬን የላብራቶሪ ናሙና መውሰድም ነበር።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ጤና ሚኒስቴር ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትም ጋር በመሆን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን ለመግታት የህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ ማስተባበሪያ ማዕከል በሟቋቋም የቫይረሱን ስርጭትና መጠን ለማወቅም ከተሰሩ ስራዎች መካከል ከአስከሬን የሚወሰድ የላብራቶሪ ናሙና መሆኑን አስታውሷል።

ሆኖም በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ የቫይረሱ የማህበረሰብ ስርጭት ከ95 በመቶ በላይ በመሆኑና ከአስከሬን ይደረግ የነበረው የናሙና ምርመራም በህዝቡም ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ሲያስነሳበትም እንደነበር ደብዳቤው ጠቅሶ በነዚህም ምክንያቶች እንዲቆም ተወስኗል።

በአሁኑ ወቅትም የብሄራዊ የኮቪድ-19 መከላከልና እና መቆጣጠር ግብረ ኃይል በወቅቱ ያለውን አለም አቀፋዊና ሃገራዊ ስርጭት ከግምት ውስጥ በማስገባትም ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ልዩ ትኩረት በመስጠትም የመከላከሉና የምርመራው ስራ ይቀጥላል ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ማንኛውንም ሞት በኮሮናቫይረስ እንደሆነ ተደርጎም በቀብር ስነ ስርአቱ ላይ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባም አሳስቧል።

ከሰባት ወራት በፊት የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ የተገኘባት ኢትዮጵያ እስከዛሬዋ እለት፣ መስከረም 19፣ 2013 ዓ.ም ባለው መረጃ በአገሪቷ ውስጥ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች 73 ሺህ 944 የደረሰ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 1 ሺህ 177 ዜጎቿን በሞት ተነጥቃለች።

በበሽታው ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 30 ሺህ 753 የደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ ለ1 ሚሊዮን 260 ሺህ 929 የላብራቶሪ ምርመራዎችን አከናውናለች።

 

#BBC

Leave a Reply