You are currently viewing ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከ2020 የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከ2020 የዓለማችን ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ተካተቱ

September 23 2020

የዘንድሮው የ“ብሪጅ ሜከር አዋርድ” አሸናፊ የሆኑት ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ከታይም መጽሔት የ2020 የዓለማችን ተጽዕኖ ፈጣሪ 100 ሰዎች ዝርዝር ውስጥ ተካትተዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተሩ ዶ/ር ቴድሮስ ከዓለማችን 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች መካከል አንዱ ሆነው ሊመረጡ የቻሉት በተለይ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሁሉም ሰው እኩል የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እንዲያገኝ በያዙት ጠንካራ አቋም ነው ተብሏል።

በተጨማሪም፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ ለመከላከል በተደረገው ጥረት የራሳቸውን አበርክቶ ማድረጋቸውም ተጠቃሽ ነው።

ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የ2020 “ብሪጅ ሜከር አዋርድ” ሽልማታቸውን በትላንትናው እለት የተቀበሉ ሲሆን ሽልማቱ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ግንባር ቀደም ሆነው እያገለገሉ ላሉ የጤና ባለሙያዎች መታሰቢያ ይሁንልኝ ሲሉ የምስጋና መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

በታይም መጽሔት የ2020 አንድ መቶ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ዝርዝር ከተካተቱት ታዋቂ ሰዎች መካከል ትውልደ ኢትዮጵያዊው አርቲስት አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊኬንድ)፣ ሌናኛዋ ትውልደ ኢትዮጵያዊት ሰአሊ ጁሊ ምሕረቱ፣ የአሜሪካ የአለርጂና የተላላፊ በሽታዎች ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶኒዮ ፋውቺ፣ አሜሪካዊቷ አቀንቃኝ ሰሊና ጎሜዝ፣ የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂፒንግ፣ የአሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተፎካካሪ ጆይ ባይደን እና የብላክ ሊቭስ ማተር መስራች አልሺያ ጋርዛ ይጠቀሳሉ።

 

Ethiopians among the Most Influential People in the world