September 20 2020
መግቢያ
በአለም ላይ የመልቲ ቫይታሚኖች ገበያ በከፍተኛ ሁኔታ እየጦዘ ይገኛል:: በአሁኑ ሰአት በአለማችን ላይ በአመት ውስጥ 30 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የሚገመት በኪኒን መልክ ያሉ ጠቃሚ ንጥረነገሮች (ሰፕሊመንቶች) ግብይት ይካሄዳል:: የዚህም ግብይት ከፍተኛ ድርሻ ከሚይዙት ሰፕሊመንቶች መካከል መልቲ ቫይታሚኖች ይገኙበታል::
ጤናማ እና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ በቀን ውስጥ የሚያስፈልጉንን ንጥረ ነገሮች በቂ በሆነ መጠን እንድናገኝ ይረዳናል:: ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ሰፕሊመንቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው::
ሰፕሊመንት (Supplement) አስፈላጊ የሚሆንባቸው ሁኔታዎች
ሰፕሊመንቶች አስፈላጊ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች በጥቂቱ:-
–ለጤነኛ ሰዎች:- በየቀኑ መልቲ ቫይታሚን ሰፕሊመንቶችን መውሰድ ጤናማ ሆኖ ለመኖር እንደሚያግዝ ጥናቶች ያሳያሉ:: በስራ ጫና ጊዜ ወይም በቂ እንቅልፍ ሳናገኝ ስንቀር አልያም በበቂ ሁኔታ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማናደርግ ከሆነ ጤናማ አመጋገብ እየተመገብን እንኳን ሰውነታችን የበላነው ምግብ ፈጭቶ ምግቡ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ወደደም ዝውውር ለመውሰድ ሊያስቸግረው ይችላል:: ለእነዚህ እና ለመሳሰሉት ሁኔታዎች ሰፕሊመንት መጠቀም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል::
– በእርግዝና ጊዜ:- በዋነኝነት በእርግዝና ጊዜ የአይረን እና ፎሌት ሰፕሊመንቶችን መውሰድ በልጁ ጀርባ አጥንት ውስጥ የሚገኙ ስሮች ላይ ሊከሰት ከሚችል አካል ጉዳትን ይከላከላል::
– መውለጃ እድሜያቸው ላለፈባቸው ሴቶች (Menopause) :- ኮልሺየም ሰሊመንትን መጠቀም መውለጃ ጊዜ ማለፍን ተከትሎ በሴቶች ላይ የሚመጣን የአጥንት መሳሳትን እና ስብራትን ይከላከላል::
– የተለያዩ ስር የሰደዱ በሽታዎች ላሉባቸው ሰዎች : – የተለያዩ ስር የሰደዱ በሽታዎች በሰውነት ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ንጥረ ነገሮችን መጠን እንዲዛባ ሊያደርጉ ይችላሉ:: በዚህ ጊዜ ሰፕሊመንቶች ለነዚህ ሰዎች ህክምና ጥቅም ላይ ይውላሉ::
–የምግብ ፍላጎት መቀነስ:- ቫይታሚን ኤ ን በበቂ ሁኔታ የሚይዙ መልቲ ቫይታሚን ሰፕሊመንቶች የምግብ ፍላጎትን ለመጨመር ይረዳሉ::
– ለህፃናት :- አንዳንድ ሰፕሊመንቶች ለህፃናት እድገት ጠቃሚ እንደሆኑ ጥናቶች ያሳያሉ:: ለምሳሌ ያህል የኦሜጋ 3 ንጥረነገር ሰፕሊመንት ለህፃናት አእምሮ እድገት ጠቃሚ እንደሆኑ በርካታ ጥናቶች አመላክተዋል:: ነገር ግን ምን ህፃናት ያህል የኦሜጋ 3 ንጥረነገር ሰፕሊመንት መውሰድ እንዳለባቸው የሀኪምን ምክር መጠየቁ ሰፕሊመንንቱ ከልክ በላይ ከተወሰደ ሊያመጣ ሚችላቸውን የጎንዮሽ ጉዳቶች ለመከላከል ይረዳል::
ከዚህ በተጨማሪም ሰፕሊመንቶች በህፃናት ላይ በተለያዩ ምክንያቶች የሚከሰቱ በሰውነት ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን እጥረት ለመከላከል ወይም ደግሞ ለማከም ይረዳል :: ለምሳሌ ተቅማጥ ያላቸው ህፃናት ዚንክ የተሰኘ ንጥረ ነገር እጥረት ያጋጥማቸዋል ለዚህም ዚንክ ሰፕሊመንት ይሰጣቸዋል::
ነገር ግን በአሁኑ ሰአት ገበያ ላይ ከሚገኙ የተለያዩ የቫይታሚን እና መአድናት ውህዶችን ከያዙ በርካታ መልቲ ቫይታሚን ሰፕሊመንቶች መሀል መርጠው ሲገዙ የሰፕሊመንቱ እቃ ላይ ካሉ ንጥረ ነገሮች መሀል ሊያጧቸው ስለማይገቡ 7 ንጥረነገሮች እንንገራችሁ::
መልቲ ቫይታሚን ሰፕሊመንቶች (Multivitamin Supplement) ሊኖሯቸው የሚገቡ 7 ንጥረነገሮች
1. ቫይታሚን ዲ (Vitamin D)
ቪታሚን ዲ ሰውነታችን ካልሺየምን አንጀታችን ውስጥ ካለው ምግብ ወደሰውነታችን እንዲሰርግ እና በሽንት መልክ ብዙ ካልሺየምን ከሰውነታችን እንዳናጣ ያግዘናል::
በቂ ቪታሚን ዲ ን አለማግኘት ለሚከተሉት የጤና እክሎች ያጋልጣል:-
- በተለያዪ በሽታዎች የመያዝ እድል ይጨምራል
- በአጥንት እና በጀርባ ህመም የመያዝ እድል ይጨምራል
- የአጥንት እና የፀጉር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማጣት
አንድ ቀላል የቪታሚን ዲ ማግኛ መንገድ ፀሃይን መሞቅ ነው:: ነገር ግን በቢሮ ስራ ተጠምደው ብዙ ጊዜያቸውን ከፀሀይ ብርሃን እርቀው የሚያሳልፉ ሰዎች እንዲሁም በቂ ፀሀይ የማያገኙ የአለም ክፍሎች ላይ የሚኖሩ ሰዎች አልያም ሰን እስክሪን ቅባቶችን ተቀብተው የፀሃይ ብርሃን ወዳለበት ቦታ የሚወጡ ሰዎች ይህን የፀሀይ ጥቅም ለማግኘት ያዳግታቸዎል::
በቪታሚን ዲ ከበለፀጉ ምግቦች መካከል
- አሳ
- እንቁላል እንዲሁም
- ወተት እና የወተት ምርቶች ( በተለይም ቪታሚን ዲ የተጨመረባቸው) ተጠቃሽ ናቸው::
ነገር ግን በቂ የፀሃይ ብርሃን የማያገኙ ሰዎች በምግብ ብቻ የማያስፈልጋቸውን የቪታሚን ዲ መጠን ማግኘት ከባድ ይሆንባቸዋል ስለሆነም ቪታሚን ዲን የያዘ መልቲ ቪታሚን ሰፕሊመንት እንዲጠቀሙ እንመክራለን::
እንደአሜሪካው ሀገራዊ የጤና ኢንስትቲዩት ( NIH) ከሆነ እድሜያቸው ከ1-13 የሆኑ ህፃናት እንዲሁም እርጉዝ እና እያጠቡ ያሉ ሴቶችን ጨምሮ እድሜያቸው ከ19-70 የሆኑ አዋቂዎች በቀን 600 IU ያክል ቪታሚን ዲ (Vitamin D) ያስፈልጋቸዋል:: እድሜያቸው ከ70 የገፋ አረጋውያን ደግሞ በቀን ውስጥ 800 IU ያክል ቪታሚንዲ ያስፈልጋቸዋል::
2. Vitamin B-12 ( ቫይታሚን ቢ – 12)
ለሰው ልጆች የሚያስፈልጉ ስምንት ገደማ የሚሆኑ የቪታሚን ቢ አይነቶች አሉ:: እነዚህን የሚይዝ ሰፕሊመንት ቪታሚን ቢ ኮምፕሌክስ ይባላል:: ከእነዚህ መሀል ቪታሚን ቢ – 12 የሰውነታችን የነርቭ እና የደም ሴሎች ጤናማ እንዲሆኑ ከማረግ ባለፈ በሰውነታችን የሚገኙ ሴሎችን ዘረመል ለመስራት ያግዛል::
የእንስሳት ተዋዕፆን የማይመገቡ ሰዎች ለ ቪታሚን ቢ – 12 እጥረት ተጋላጭ ናቸው:: ይህም የሚሆነው ቪታሚን ቢ – 12 በአብዛኛው የሚገኘው ከእንስሳት ተዋዕፆ ማለትም ከስጋ ከወተት ምርቶች ከአሳ ከእንቁላል ወዘተ ስለሆነ ነው:: ስለዚህ ቬጋን ወይም ቬጂቴሪያን ከሆኑ ቪታሚን ቢ – 12 የሚይዙ ሰፕሊመንቶችን እንዲጠቀሙ ይመከራል::
ሰውነታችን በቀን ውስጥ የሚያስፈልገው የ ቪታሚን ቢ – 12 (Vitamin B12) መጠን ከ3 ማይክሮ ግራም ያነሰ ነው:: ስለዚህም ባለሙያዎች በአንድ ጊዜ ለመብል የሚውል ( Serving Size) ከ1-2 ማይክሮ ግራም የሆነ መልቲ ቪታሚን ሰፕሊመንት መጠቀምን ይመርጣሉ ምክንያቱም ከዛ የተረፈው የቪታሚኑ መጠን በሽንት መልክ ስለሚወገድ ነው::
3. ካልሺየም (Calcium)
የአሜሪካ ህዝብ ከ 40 % በላይ የሚሆነው በምግብ ውስጥ በቂ ካልሺየም አያገኝም:: በኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰራ ጥናት ባናገኝም ብዙ የኢትዮጵያ ህዝብ በቂ የካልሺየም መጠን በምግብ ውስጥ እንደማያገኝ ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም:: ይህ ማለት ሰዎች ለአጥንታቸው እና ለጥርሳቸው ጥንካሬ የሚረዳን ንጥረነገር በበቂ ሁኔታ እያገኙ አይደለም ማለት ነው:: . ሴቶች የመውለድ እድሜያቸው ካለፈ በኋላ የሰውነት አጥንታቸው እየተሸረሸረ ጥንካሬውን እያጣ ይመጣል ስለዚህም ከወንዶች በበለጠ ሴቶች የካልሺየም ሰፕሊመንት ያስፈልጋቸዋል ማለት ነው::
ካልሲየምን የሚይዙ የምግብ አይነቶች
- ወተት እና የወተት ውጤቶች
- ካልሺየም የተጨመረባቸው ጥራጥሬዎች
- አሳ
- ኦቾሎኒ ወዘተ…
በነዚህ ምግቦች የበለፀገ አመጋገብ ካለዎ የሚያስፈልጎትን የካልሺየም መጠን እያገኙ ነው ማለት ነው::
አንድ ጤነኛ አዋቂ ሰው በቀን 1000 ሚ.ግ ገደማ ካልሺየም ማግኘት አለበት:: ካልሺየም የያዘን መልቲ ቪታሚን ሰፕሊመንትን ሲጠቀሙ ሰፕሊመንቱ የያዘው ካልሺየም በካልሺየም ሲትሬት መልክ ቢሆን መልካም ነው::
4. አይረን (Iron)
መልቲ ቫይታሚኖ ውስጥ አይረን ቢያስፈልጎትም ሁሉም ሰው እኩል የአይረን መጠን ያስፈልገዋል ማለት አይደለም:: ከአይረን ጥቅሞች መሃል:-
- ጉልበት ለመጨመር
- የአእምሮን ብቃት ለመጨመር
- ጤናማ ቀይ የደም ሴሎች እንዲኖሩን
ቀይ ስጋን የምንመገብ ሰዎች ከሱ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን የአይረን መጠን በሚገባ ማሟላት እንችላለን:: ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች ላይ ማለትም በእርግዝና ጊዜ የወር አበባ ላይ ሲሆኑ ወዘተ… ሰውነት የሚያስፈልገው የአይረን መጠን ከፍ ሊል ይችላል:: በተጨማሪም ልጆች በጉርምስና (puberty) እድሜ ላይ ሲሆኑ ፈጣን እድገት ስለሚኖራቸው የሚያስፈልጋቸው የአይረን መጠን ከፍ ሊል ይችላል ::
የእንስሳት ተዋእፅኦን የማይመገቡ ሰዎች በሚወስዱት መልቲ ቫይታሚን ውስጥ አይረን ቢኖረው ይመከራል ምክንያቱም በአይረን የበለፀጉ በተለይም የስጋ ውጤቶችን ሰውነታቸው አያገኝም::
ሰፕሊመንት ሲገዙ 18 ሚግ ገደማ አይረንን በ አይረን ሰልፌት (ferrous sulfate) አይረን ግሉኮኔት (ferrous gluconate) ፌሪክ ሲትሬት ( ferric citrate) ወይም ፌሪክ ሰልፌት(ferric sulfate) መልክ የያዘን ፈልገው ይግዙ::
5. ማግኒዢየም (Magnesium)
ማግኒዢየም ብዙ የሚታወቀው ለአጥንታችን ጤና እንደሚጠቅም እና የሰውነታችን ሀይል የማምረት ሂደት ላይ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ነው :: ነገር ግን ማግኒዢየም ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች በዛ ያሉ ጥቅሞች አሉት ከእነዚህም መሀል ጭንቀትን መቀነስ እና የነርቭ ስሮአታችንን ማረጋጋት እንቅልፍ የመተኛት ችግርን በተወሰነ መልኩ ማቃለል የነርቮቻችን እና የጡንቻዎቻችን ስራዎችን መቆጣጠር የደም ውስጥ የስኳር መጠንን መመጠን ዘረመል ፕሮቲን እና አጥንትን መስራት ወዘተ ይገኙበታል ::
ብዙ ሰዎች የማግኒዚየም እጥረት ያጋጥማቸዋል ምክንያቱም ንጥረነገሩን የሚይዙ የምግብ አይነቶችን በማገባ ስለማይመገቡ ነው:: በማግኒዚየም የበለፀጉ የምግብ አይነቶችን ለማንሳት ያህል
- ዱባ
- አተር
- ኦቾሎኒ
- ቡኒ ሩዝ
- ስፒናች ወዘተ… ይገኙበታል::
ስለዚህ እነዚህን ምግቦች በደንብ የሚመገቡ ጤናማ ሰዎች በማግኒዚየም የበለፀገ ሰፕሊመንት እንብዛም አስፈላጊ ላይሆን ይችላል::
ሰፕሊመንት ያስፈልገኛል ብለዉ የሚያስቡ ከሆነ የማግኒዚየም መጠኑ ከ300-320 ሚግ የሆነን መልቲ ቪታሚን ሰፕሊመንት ይጠቀሙ::
6. ዚንክ (Zinc)
ዚንክ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምን ያጎለብታል በተጨማሪም ሰውነታችን የወሰድናቸውን ሀይል ሰጪ ምግቦች በሚገባ ጥቅም ላይ እንዲያውል ይረዳል::
እንዲሁም ዚንክ ቁስል ቶሎ እንዲሽር በማገዝ ረገድ ከፍ ያለ ሚና ይጫወታል::
ሰውነት ውስጥ ያለ የዚንክ መጠን እድሜያቸው የገፋ ሰዎች ላይ እና በተለያዩ ምክንያቶች ከፍተኛ የአእምሮ ጫና ባለባቸው ሰዎች ላይ ሊወርድ ይችላል:: ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በቪታሚን ሰፕሊመንታቸው ውስጥ ዚንክ ቢኖር ይመረጣል ::
ዚንክን የሚይዙ የምግብ አይነቶች:-
- ስጋ
- ስፒናች
- ሰርዲን
- ቡኒ ሩዝ
- የዱባ ፍሬ ወዘተ…
ዚንክ ሰፕሊመንታችን ውስጥ መኖር አለበት ያልንበት አንድ ወሳኝ ምክንያት ሰውነታችን ዚንክ አጠራቅሞ ማስቀመጥ ስለማይችል ነው:: ይህም ዚንክን የሚይዙ የምግብ አይነቶችን በየጊዜው ካልተመገብን የሰውነታችን ዚንክ መጠን ሊያንስ ይችላል::
መልቲ ቪታሚን ሰፕሊመንት ሲገዙ በውስጡ ከ5-10 ሚግ ዚንክ እንዳለው ያረጋግጡ::
7. ፎሌት (ቪታሚን ቢ 6) / Vitamin B6
ፎሌት ሲባል ብዙዎቻችን ቶሎ የሚመጣልን ሴቶች በእርግዝና ወቅት በልጁ ላይ ሊከሰት የሚችልን አካል ጉዳተኝነትን (Birth defect) ለመቀነስ የሚወስዱትን ነው:: ነገር ግን ፎሌት የአእምሮ ድብታን (Depression) የሰውነት መቆታትን (Inflammation) ለመቀነስ ወዘተም… ይጠቅማል::
ፎሌት ከሚይዙ የምግብ አይነቶች መሀል አቮካዶ ጠቆር ያሉ አረንጓዴ ቅጠላ ቅጠል ምግቦች ባቄላ ሎሚ ብርቱካን ወዘተ … ይገኙበታል::
ሰባቱንም ንጥረነገሮች የሚያሟሉ መልቲ ቫይታሚን ሰፕሊመንቶች:
✔️ BayBerg’s Women’s Multivitamins, $15.87
✔️ Naturelo Whole Food Multivitamin for Men, $42.70
✔️ Centrum Adult Multivitamin, $10-25
መደምደሚያ
✔️ በመልቲ ቫይታሚን ላይ ግን ጥገኛ አይሁኑ
✔️ በቂ የተመጣጠነ ምግብ የምንጠቀም ከሆነ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን የቪታሚን እና ማዕድናት መጠን ከምንበላቸው ምግቦች ላይ መዝብሮ የማውጣት ብቃት አለው::
✔️ ሰፕሊመንቶች ምግብን አይተኩም
✔️ ሰፕሊመንቶች ጠቃሚ ተጨማሪ የመአድናት ምንጭ ናቸው እንጂ ማንኛውም መልቲ ቫይታሚን ሰፕሊመንት ምንም ያህል ማስታወቂያው ቢያምር ምግብን አይተካም::
Source :-
✔️ Harvard
Click Here For More Health Products Reviews