You are currently viewing የኮቪድ-19 መድኃኒቶች ምርምር በኢትዮጵያ‼️

የኮቪድ-19 መድኃኒቶች ምርምር በኢትዮጵያ‼️

468x60 Healthy Weight Loss Delivery Plan
September 19 2020

Doctorsonlinee.com ; የኮቪድ-19 መድኃኒቶች ምርምር በኢትዮጵያ

የኮቪድ-19 መድኃኒቶች ምርምር በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ‘ኮሮናቫይረስን ( ኮቪድ-19) ሊያክሙ ይችላሉ’ ተብለው በቀረቡ አምስት መድኃኒቶች ላይ ምርምር እየተደረገ መሆኑን የሕብረተሰብ ጤና ተቋም የባህልና ዘመናዊ መድኃኒት ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ወርቁ ገመቹ ገልፀዋል።

አቶ ወርቁ እንዳሉት ከባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማኅበር በኩል ‘ለኮቪድ-19 ይሆናሉ የተባሉ’ ከ50 በላይ መድኃኒቶች ለተቋሙ ቀርበዋል።

ነገር ግን በአቅምና በሰው ኃይል ውስንነት ምክንያት ከእነዚህ መካከል 5 ያህሉን መርጠው መመልከታቸውንና ጥናት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
ባህላዊ መድኃኒቶቹ በጭስ መልክ የሚታጠን፣ በሻይ መልክ የሚጠጣ፣ በቅባት መልክ የቀረበ፣ በምግብ መልክ የሚወሰዱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ምርምር እንዲደረግባቸው መቅረባቸውን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በጭስ መልክ የቀረበውን በላብራቶሪ ደኅንነቱን ለማጥናት ስለማይቻል ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
በመሆኑም የተመረጡት አምስቱ ባህላዊ መድኃኒቶች በሻይ መልክ፣ በምግብ መልክ፣ በቅባት መልክ ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ መሆናቸውን አቶ ወርቁ ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው የጥናት ሂደትም ለመድኃኒቶቹ ጥቅም ላይ የዋሉትን የእፅዋት ዓይነቶችና ዝርያቸውን መለየታቸውንና ተያያዥ የጽሁፍ ዳሰሳ [Literature Review] በማድረግ መረጃው ተሰንዶ ወደ ቀጣይ ሂደት ለመሻገር ዝግጅት ላይ መሆናቸውን አቶ ወርቁ አስረድተዋል።
መድኃኒቶቹ ከአምስት ሰዎች የመጡ ቢሆንም ከ30 በላይ እፅዋት እንደተካተቱበት የጠቀሱት አቶ ወርቁ፤ ለ30ዎቹ የእፅዋት ዓይነቶችም የተያያዥ ጽሁፍ ዳሰሳ መስራታቸውን ተናግረዋል።
በዳሰሳውም “የእፅዋቱን ምንነት፣ ተመሳሳይ ስም ያላቸውን የመለየት፣ አካባቢያዊ ስም መኖር አለመኖሩን የማጥራት፣ በአገር አቀፍም ሆነ በዓለም ዙሪያም የእፅዋቶቹ መገኛ የት እንደሆነና ለምን እንደሚጠቀሙባቸው የማጥናትና የመለየት ሥራ ተከናውኗል” ብለዋል።

ሰዎች እነዚህን እፅዋቶች ለምግብነት የሚጠቀሙባቸው መሆን አለመሆናቸውንም በዳሰሳው አረጋግጠዋል።

እፅዋቶቹ በውስጣቸው ምን ዓይነት ኬሚካሎች ይዘዋል የሚለውን በተመለከተም በሳይንሳዊ መንገድ ጥናት ተካሂዶባቸው መሆን አለመሆኑ፤ እንዲሁም ደኅንነታቸውንና የጎንዮሽ ጉዳት ካላቸው መለየትና ሰው ላይ ተሞክሮ እንደሆነ በዳሰሳቸው ተመልክተዋል።

ነገር ግን እስካሁን ሰው ላይ የተሞከረ አለማግኘታቸውን አቶ ወርቁ ተናግረዋል።

በዚህ ጥናት ምን ተገኘ?

አቶ ወርቁ እንደተናገሩት አስካሁን በተደረጉት የጽሁፍ ዳሰሳ ጥናታት የደደረሱበት እነዚህ ባህላዊ መድኃኒቶች የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ወይም ለማከም የሚጠቅሙ ሆነው አለማግኘታቸውን ነው።

ይሁን እንጂ የተለያዩ በሽታዎችን ለመፈወስ በባህላዊ መልክም ጥናትን የተካሄደባቸው አሉ። ለምሳሌ የሰውነት ሙቀትን የሚቀንሱ፣ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚጨምሩ፣ የምግብ ፍላጎትን የሚጨምሩ ሆነው እንዳገኟቸው ገልፀዋል።

ምርምሩ ማንን ያሳትፋል?

በምርምር ሂደቱ እየተሳተፉ ያሉት በዋናነት የባህል መድሃኒት አዋቂዎቹ፣ የተቋሙ ተመራማሪዎች እና ናዲክ (ብሔራዊ የእንስሳት ጤና ምርምርና ጥናት ማዕከል) ናቸው።

በመድኃኒት ምርምሩ ላይ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተወጣጡ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን፤ በውጭ ከሚገኘው ናዲክ የምርምር ተቋም ያሉ ባለሙያዎችም በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንደሆኑ ዳሬክተሩ አስረድተዋል።

ምርምሩ ምን ያህል ተስፋ ሰጪ ነው?

በዚህ የምርምር ደረጃ ላይ ሆኖ ኮሮናቫይረስን ማዳን አለማዳኑን እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደማይችል ዳሬክተሩ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም የተለያዩ እፅዋቶች የተለያዩ በሽታዎችን ይፈውሳሉ ተብለው ሙከራ መካሄዱን ጠቅሰው፣ ቢሆንም ግን በሽታውን ሳይሆን የበሽታውን ምልክቶች ላይ ለውጥ ያመጡ እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ከመካከላቸው ግን የሚፈውሱም እንደነበሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም መድኃኒቶቹ “የበሽታ ምልክቶችን ሊያጠፋ ይችላል፤ ነገር ግን ይህ በሳይንሳዊ መንገድ መረጋገጥ አለበት። በመሆኑም ተስፋ የለውም ወይም አለው ማለት ይከብዳል” ብለዋል አቶ ወርቁ።

የምርምሩ ቀጣይ ሂደት ምንድን ነው?

አቶ ወርቁ እንደገለፁት ከሆነ ከቤተ ሙከራ ውጪ ያሉ ሥራዎችን አጠናቀው ወደ ቤተ ሙከራ ምርምር ለመግባት የቤተ ሙከራ እንስሳትን እያራቡ መሆኑን አመልክተዋል።
በመሆኑም እነዚህ እንስሳት አካለ መጠናቸውና እድሜያቸው ለላብራቶሪ ሙከራ ብቁ ሲሆን እነርሱ ላይ ሙከራ መደረግ ይጀመራል ብለዋል።


ስለዚህ በሕብረተሰብ ጤና ተቋም ውስጥ የደኅህንነት ሥራው የሚሰራ ሲሆን የመድኃኒቶቹ የፈዋሽነት ወይም የፍቱንነት ሥራው ግን በሽታው አዲስ ከመሆኑና ከዚህ በፊት በተቋሙ ተሰርቶ ስለማይታወቅ ‘ናዲክ’ ከተባለ የምርምር ተቋም ጋር በጋራ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት ይህ የሚሆነው መጀመሪያ ላይ የመድኃኒቱ የደኅንነት ሁኔታ [ምን የጎንዮሽ ጉዳት አለው የሚለው] ሲጠናቀቅ ነው።

ምርምሩ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ ይችላል?

እንደ አቶ ወርቁ ገለፃ በመድኃኒት ጥናት የሚደረገው የደኅንነት ፍተሻ አኪዩት (Acute) ለቤተ ሙከራ እንስሳቱ መድኃኒቱ ከተሰጠ በኋላ የሚደረግ ክትትል 14 ቀናትን ይወስዳል።

ሌላው የደኅንነት ጥናት ሰብ አኪዩት (Sub Acute) ደግሞ 28 ቀናት ይፈጃል። ሌላኛው ሂደት ክሮኒክ የሚባል ሲሆን 90 ቀናት ወይም ሦስት ወራትን ይጠይቃል። ከዚህ ባሻገርም 6 ወራትም የሚያስፈልገው ሂደት ይኖራል። በዚህ ሂደት እንስሳቱ ላይ የታየው የጎንዮሽ ጉዳት ይጠናል።

“አንድ ሰው በኮቪድ-19 በሽታ ከተያዘ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይድናል ወይም ይሞታል። በመሆኑም 28 ቀናት የሚወስደውን ሰብ አኪዩት የተባለ የደህንነት ጥናት መርጠናል” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በዚህ ሂደትም ለእንስሳቱ ብቻ 28 ቀናት ይሰጣል። ከዚያም እነርሱን ለማጥናት እስከ 40 ቀን እንደሚወስድ ጨምረው ገልጸዋል።

ይህ ከሆነ በኋላ ውጤቱ ታይቶ ፍቱንነቱ ወይም ፈዋሽነቱ ወደሚረጋገጥበት ደረጃ ይሸጋገራል። በዚህ ሂደት ጥራቱና ደረጃው ከተጠበቀ በኋላ ወደ ክሊኒካል ሙከራ እንደሚያመራ ሂደቱን አብራርተዋል።

አንድ መድኃኒት ከመጀመሪያው ጀምሮ ለሰው ጥቅም እስከሚውል ድረስ ከ3 አስከ 14 ዓመታት ድረስ እንደሚፈጅ አመልክተው “ሳይንስ ስለሆነ አቋራጭ መንገድ የለም፤ ስለዚህ በዚህ ሂደት ማለፍ አለበት” ብለዋል።

የኢኖቪሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መጋቢት ወር ገደማ የባህል ሕክምና አዋቂዎችን ከዘመናዊው ጋር በማጣመር ለኮሮናቫይረስ ሕክምና የሚያገለግል ተስፋ ሰጪ አገር በቀል መድኃኒት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቆ ነበር።

መድኃኒቱም መሠረታዊ የምርምርና ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሂደቶች ማለፉን በወቅቱ ተገልፆ ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ ለበርካቶች ተስፋ የሰጠ ቢሆንም “ምንም ባልተያዘበት ሰው ራሱን እንዳይጠብቅ ያዘናጋል” ሲሉ ብርቱ ትችቶች መሰንዘራቸው አይዘነጋም።

በኢትዮጵያ እስካሁን ከ66 ሺህ በላይ ሰዎች በኮሮናቫይረሱ ተያዙ ሲሆን 1060 ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ሕይወታቸው አልፏል።

ምንጭ፦ BBC አማርኛ

For More Health related News Click Here 

 

To Get alerts of latest Health Related news  Go-to Our Telegram Channel  

 

 

Leave a Reply