ዓለም ተስፋ የጣለበት የኦክስፎርድ የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር እንዲቆም ተደረገ‼️

September 9 2020

የመጨረሻ የክሊኒካል ሙከራ ላይ የነበረውና ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የቆየው የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ከመድሃኒት አምራቹ አስትራዜኔካ ኩባንያ ጋር እያበለጸጉት የነበረው የ ኮሮና ቫይረስ ( ሳርስ-ኮቭ 2) ክትባት ነበር።

ምርምሩ ለጊዜው ባለበት ይቁም ተብሏል። ምክንያቱ ደግሞ የክትባት ቅንጣቱን የወሰዱ በጎ ፍቃደኛ ተሳታፊዎች ህመም ስላጋጠማቸው ነው።

ይሁን እንጂ ግዙፉ የመድኃኒት አምራች አስትራዜኔካ ይህ የሚያደናግጥ ሳይሆን የሚያጋጥም ነው ይላል።

ህመም የተሰማቸው ተሳታፊዎች ለምን ህመም እንደተሰማቸው ለማወቅ ጊዜ ይፈልጋል።

የኦክስትፎርድና የአስትራዜኔካ የምርምር ውጤት የዓለም አገራት ትንፋሻቸውን ውጠው በጉጉት ሲጠብቁት የነበረ ነው።

በዓለም ላይ በክትባት ሙከራ ውስጥ እያለፉ ካሉ ደርዘን ከሚሞሉ የምርምር ሥራዎች ሁሉ ይህ ግዙፉና ተስፋም የተጣለበት ነበር። ቀድሞ ለሕዝብ ይደርሳል፣ ዓለምን ይታደጋል ተብሎም ነበር።

ይህ የኦክስፎርድና አስትራዜኔካ የጥምረት የክትባት ምርምር ምዕራፍ 3 ደርሶ ነበር። ይህም ማለት ዋናዎቹን የምዕራፍ 1 እና 2 አልፎ፣ ፈዋሽነቱ ተረጋግጦ በብዙ ቁጥር ሰዎች ላይ መሞከር የጀመረ ማለት ነው።

በአሜሪካ፣ በዩኬ፣ በደቡብ አፍሪካና በብራዚል የሚገኙ 30ሺ ሰዎች ይህንን ክትባት እንዲወስዱ ተደርጎ ምን ዓይነት ምልክት እንደሚያሳዩ እየተጠበቀ ነበር።

ምዕራፍ 3 የመድኃኒት ሙከራዎች በርካታ ሺህ ሰዎች የሚሳተፉባቸው ከመሆናቸው ባሻገር ዓመታትን ይወስዳሉ።

አሁን ባለው የዓለም ጉጉት ግን አመታት ይጠበቃሉ ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።

እንዲህ ዓይነት ነገር ሲያጋጥም በሕክምናው ዓለም አዲስ አይደለም።

3ኛ ምዕራፍ የደረሱ የመድኃኒት ሙከራዎች ተሳታፊዎች የተለየ ሕመም ሲያጋጥማቸው ለጊዜው እንዲቆሙ ይደረጋል። አሁን የሆነውም ይኸው ነው።

ከዚህ በኋላ ገለልተኛ የተመራማሪዎች ቡድን በጉዳዩ እንዲገባ ይደረጋል። የተወሰዱ ጥንቃቄዎችን ከፈተሸ በኋላ ሁሉም ሂደቶች ትክክል ነበሩ ተብሎ ሲታሰብ የመድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ሙከራውና ምርምሩ እንዲቀጥል ሊወስን ይችላል።

“እንዲህ ሰፊ በሆኑ ሙከራዎች በተሳታፊዎች ላይ ህመም መከሰቱ አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን ገለልተኛ ወገን ሊያጣራው ይገባል” ብለዋል የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ቃል አቀባይ።

የኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ምርምሩን ለጊዜው እንዲያቆም ሲደረግ ደግሞ ይህ የመጀመርያው አይደለም። ከተሞከረባቸው ሰዎች የተወሰኑት አሟቸው ሆስፒታል ሲገቡ ምርምሮች ሁሉ ባሉበት ይቆማሉ። ይህ የተለመደ አሰራር ነው ይላል፣ የቢቢሲ የጤና ጉዳዮች ዘጋቢ።

እንዲያውም ምርምሩ በጥቂት ቀናት ውስጥ ይቀጥል ሊባልም ይችላል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መድኃኒቱን ከኅዳር 3 ምርጫ በፊት አጥብቄ እፈልገዋለሁ ሲሉ ነበር።

 

#BBC

 

Subscribe to Receive Free Updates
Loading

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Copy link
Powered by Social Snap