You are currently viewing ሞትን አይቼ ተመለስኩ‼️ :- ከኮቪድ-19 ያገገመው ሰው ማስታወሻ

ሞትን አይቼ ተመለስኩ‼️ :- ከኮቪድ-19 ያገገመው ሰው ማስታወሻ

September 8 2020

ከኮቪድ-19 ያገገመ ሰው አጭር ታሪክ

የ27 ዓመት ወጣት ነኝ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ሽሮ-ሜዳ አካባቢ ነው የምኖረው፡፡ አስታውሳለሁ ቀኑ ሰኔ 16 ሐሙስ ዕለት ነው፤ ካለወትሮዬ ምቾት የሚነሳ ስሜት ተሰማኝ፡፡ ቀኑን ሙሉ እንዲሁ ስረበሽ ነበር የዋልኩት፡፡ ማታ ላይ ምግብ ባያሰኘኝም በግድ ቀምሼ ተኛሁ፡፡

እኩለ ሌሊት ብን ብን የሚል ደረቅ ሳል ድንገት ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ፤ ሰውነቴም በሚነድ እሳት ውስጥ እንዳለ ሆኖ አገኘሁት፡፡ ባኞ ቤት ገባሁና በቀዝቃዛ ውሃ ፊቴን ታጠብኩ ሊበርድ አልቻለም፡፡ አፌ ስለደረቀና ስለመረረኝ በውሃ ተጉመጠመጥኩት፤ እንደማቅለሽለሽ አለኝ፡፡

ተከራይቼ ስለምኖር በወቅቱ አጠገቤ የሚረዳኝ ሰው አልነበረምና እማደርገው አጣሁ፡፡ ቆይቼ ለጓደኛዬ ደውዬ እንደታመመኩ ነገርኩት፡፡ መኪና ይዞ መጣና ወደ አቅራቢያዬ ወደሚገኝ ጤና ጣቢያ ወሰደኝ፤ እነሱም ሁኔታውን አይተው ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ላኩኝ፡፡

የሆስፒታሉ ሃኪሞችና ነርሶች ተረባረቡና አስገቡኝ፡፡ ወዲውኑ ምርመራ ታዞልኝ ናሙና እንድሰጥ ተደረገ፡፡ ትኩሳቱ እየጨመረ መጣ፤ አጠገቤ የሚረዱኝን የጤና ባለሙያዎች ጭምር የሰውነቴ ግለት ይታወቃቸው ነበር፡፡ ቀስ በቀስ እየደከመኝ እየደከመኝ መጣ፡፡
የምርመራ ውጤቴ ደረሰ፤ ውጤቱም የኮቪድ-19( የ ኮሮና ቫይረስ ) በሽታ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ ከዚያ በኋላ የሆንኩትን ሁሉ በውል አላቀውቅም ነበር፡፡

ከ7 ቀናት በኋላ ከሰመመን ስሜቴ ወጥቼ ራሴን ሳውቅ በአፍንጫዬ ቱቦ እና በእጄ ላይ ደግሞ ግሉኮስ ተተክሎልኛል፤ በዙሪያዬ ደግሞ መላ አካላቸውን በተሸፈኑ ጤና ባለሙያዎች ተከብቤ አገኘሁት፡፡ ድንጋጤ አይሉት የመረበሽ ሰሜት ተሰማኝ፤ ከአጠገቤ የነበረ ሃኪም ሊያረጋጋኝ ሞከረ፡፡ አይኖቼ በእምባ ተሞሉ፡፡

ቀስ በቀስም ራሴን እያወቅሁ ስሄድ ወደኋላ እንደህልም ያየሁትን ማስታወስ ጀመርኩ፤ ነጭ የለበሱ የለበሱ ሰዎች አጅበውኝ ይዘውኝ ሲሄዱ ያየሁት ታወሰኝ፡፡ ሰፊ አዳራሽ ያለው ዙሪያ ገባው በአበቦች ያጌጠ ውብ ቦታም ይታወሰኛል፡፡ እንዲህ አይነት ስፍራ በምድር ላይ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤ ምንድን ነው ነገሩ ብዬም ራሴን ጠየኩ፡፡

በተደረገልኝ ህክምናና እንክብካቤ ራሴን በደንብ እያወኩኝ ስመጣ ያ ያየሁት ነገር በሞትና በህይወት መካከል የነበርኩበትን ወቅት በማስታወስ ላይ እንደነበርኩ ተረዳሁ፡፡ ሳልሞት ሞትን አይቼ እንድመለስ የረዳኝን ፈጣሪ እጅግ አድርጌ አመሰግነዋለሁ፡፡

እኛ የምናውቀው በሽታ ሲያመን ሰው እንዳያስታምመንና እንዳይጠይቀን እስከ መከልከል የሚያደርስ አልነበረም፡፡ ኮሮና ግን የተለየ ነው፤ ቤተሰብ እንኳ ከጎኔ ሆኖ እንዲያስታምመኝ ያለፈቀደልኝ ጨካኝ በሽታ ነው፡፡

ከምንም በላይ ግን የህክም እርዳታና እንክብካቤ ያደረጉልኝን የጤና ባለሙያዎች በእጅጉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ፤ በህይወት ዘመናቸው ሁሉ ክፉ አይንካቸው፡፡
ቀድሞ ያልታዬኝ ስህተቴ አሁን ላይ ቁልጭ ብሎ ታይቶኛል፤ ለበሽታው የነበረኝ ግዴለሽነት ዋጋ አስከፍሎኛል፡፡ እኔ እድሉን አግኝቼ ታክሜ መዳኔ ቢያስደስተኝም አሁን ላይ ጤና ተቋማት ወደ መጨናነቅ ደረጃ እየደረሱ መሆኑን ስሰማ በእጅጉ አሳዝኖኛል፤ ችግሩን ቀምሸዋለሁና፡፡ እናም ወገኖቼ ከእኔ ተማሩ፤ በተቻለ መጠን ጥንቃቄ በማድረግ ከኮሮና በሽታ ራሳችንና ቤተሰባችንን እንጠብቅ መልዕክቴ ነው፡፡
(ከኮቪድ-19 በሽታ ያገገመ ግለሰብ ታሪክ፤ ስሙ በግል ጉዳዩ ምክንያት ያልተጠቀሰ)
#COVID19Ethiopia

 

Source: EPHI

 

[email-subscribers-form id=”1″]

Leave a Reply