ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ( ኮቪድ-19) መመርመሪያ ኪት ማምረት ልትጀምር ነው፡- ጤና ሚኒስቴር

September 6 2020

በኢትዮጵያ የ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ-19) መመርመሪያ ኪት ከአንድ ወር በኋላ ማምረት እንደሚጀመር የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ለኢዜአ እንደተናገሩት ኮሮና ቫይረስን ( ኮቪድ-19ን) የመመርመር አቅምን ከፍ ለማድረግ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ከአንድ ወር በኋላ ከቻይና መንግሥት ጋር በመተባበር የመመርመሪያ ኪት ለማምረት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለእዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ድጋፉን ከምታደርገው የቻይና መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ እየመከሩ መሆኑን ገልጸዋል።

“የመመርመሪያ ኪቱን በአገር ውስጥ ማምረት ሲጀመር ከውጭ የሚገባውን ኪት ሙሉ በሙሉ ያስቀራል” ያሉት ዶክተር ደረጀ፣ ምርቱ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት እንደሚዳረስም ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ በየጊዜው እያደገ የመጣውን የመመርመር አቅም በእጅጉ ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት የኢንፌክሽን መከላከያ ግብዓቶች በኢትዮጵያ በስፋት መመረት መጀመራቸውን ጠቁመው፣ የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሶችን ወደ ውጭ አገራት መላክ መጀመሩንም ገልጸዋል።

በሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክ እነዚህን ቁሶች የሚያመርቱ ኩባንያዎች ቀዳሚ መሆናቸውን ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 52 የኮሮናቫይረስ መመርመሪያ ማዕከላት የሚገኙ ሲሆን በእነዚህም በቀን ከ20 ሺህ በላይ ናሙናዎችን መመርመር ተችሏል።

Subscribe to Receive Free Updates
Loading

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Share via
Copy link
Powered by Social Snap