You are currently viewing ተቅማጥ ወይም ትውከት በህፃናት ላይ ሲከሰት ችላ ሊባል አይገባም‼️

ተቅማጥ ወይም ትውከት በህፃናት ላይ ሲከሰት ችላ ሊባል አይገባም‼️

September 5 2020

የተቅማጥና ትውከትን የሚያመጡ ነገሮች ምንድን ናቸው?

በህፃናት ላይ የሚከሰት ተቅማጥና ትውከት ብዙውን ጊዜ በተለያዩ በጥቃቅን በዓይን በማይታዩ ተዋህሲያን እንደ ቫይረስ ፣ ባክቴሪያ ወይም የባክቴሪያ መርዞች አማካይነት ይከሰታል::
ይህም ከንጽህና መጓደል ጋር ተያይዞ በተለይም በተህዋሲያን በተበከሉ ምግቦች፣ የመጠጥ ውሃ እና በሌሎች መተላለፊያ መንገዶች ከሰው ወደ ሰው በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፍ ነዉ፡፡
በተጨማሪም ከተዋህሲያን ባለፈ አንዳንድ መድሃኒቶች ተቅማጥ ሊያስከትሉ ይችላሉ። ስለዚህ ልጆች አዲስ መድሃኒቶችን ከጀመሩ በኃላ ተቅማጥ ከያዛቸው በመድሃኒቱ አማካኝነት ሊሆን ስለሚችል ስለመድሀኒቱ ጎንዮሽ ጉዳቶች ከሀኪም ጋር መምከር ተገቢ ነው።

የተቅማጥና ትውከት ያላቸው ልጆች በሰውነታቸው ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ መጠን እንደመነመመነ የሚያሳዩ ወሳኝ ምልክቶች አሉ እነዚህም:-
✔️ መጠነ ብዙ የሆነ ውኃማ ተቅማጥ
✔️ ተደጋጋሚ ትውከት
✔️ የአይን መስርጐድ
✔️ የአፍና የምላስ መድረቅ
✔️እንባ አልባ መሆን
✔️ የሽንት መጠን መቀነስ
✔️ የቆዳ ድርቀትና መሸብሸብ በመጨረሻም ከፍተኛ የሆነ የሰውነት ድርቀት በማስከተል ህፃኑ በወቅቱ ካልታከመ ለሞት ሊያበቃው ይችላል፡፡

ተቅማጥና ትውከት የሚያስከትለው ችግር ምንድነው ?

በተቅማጥና ትውከት የተያዘ ህፃን ከሰውነቱ ብዙ ፈሳሽ ስለሚወጣ በሽተኛው የሰውነት ድርቀት /Dehydration/ ያስከትልበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በልጁ ሰውነት ውስጥ የሚገኙ ንጥረ ነገሮች መጠን እንዲዛባ ያደርጋል:: ይህ ሁኔታ ደግሞ በተቅማጥና ትውከት የተያዘው ህፃን በአጭር ጊዜ ራሱን መሳትን ጨምሮ ሌሎች የነርቭ ስርአት መዛባት ምልክቶች እንዲኖሩት ያደርገዋል፡፡ ልጁ በጊዜ አስፈላጊው የሕክምና ዕርዳታ ከተደረገለት የመሞት እድሉ እጅግ ኢምንት ነው። ነገር ግን አፋጣኝ የሕክምና ዕርዳታ ካላገኘ በበሽታው የመሞት እድሉ ይጨምራል፡፡

በሽታውን መለያ መንገዶች?

1. ምልክቶቹን በማየት
2. በላብራቶሪ ሊረጋገጥ ይችላል፡፡

የተቅማጥ በሽታ እንዴት ይታከማል ? 

👉  አንድ ልጅ ተቅማጥ ወይም ትውከት ካለው ወደጤና ተቋም መውሰድ ተገቢ ነው::
👉 የተቅማጥ ዋናው ህክምና በተቅማጡ ምክንያት ከሰውነታችን ውስጥ የጎደለውን ውሃ፣ጨውና ስኳር መተካት ነው። ይህንንም ለማድረግ:-ORS (ኦአርኤስ) የተባለውን መድሃኒት ከፋርማሲ ገዝቶ በንፁህ ውሃ በጥብጦ መጠጣት ወይም የልጁ የሰውነት ውሃ መጠን እጅጉን ካነሰ በጤና ተቋማት በደም ስሩ በኩል በሚሰጡ ፈሳሾች ነው ::
ኦአርኤስን አዘገጃጀት ከጤና ባለሞያ መረዳት ይችላሉ።
👉 ኦአርኤስን በአካባቢዎ ማግኘት ካልቻሉ ግን ራስዎ በቤትዎ ማዘጋጀት ይችላሉ። ይህንንም ለማድረግ አንድ ሌትር ንፁህ ውሃ ውስጥ 1 የሾርባ (ትልቅ) ማንኪያ ጨው እና 5የሾርባ (ትልቅ) ማንኪያ ስኳር ጨምሮ በጥብጦ በማዘጋጀት መጠጣት ይቻላሉ።
በተጨማሪም በሽታውን እንዳመጣው ተዋህሲ አይነት በባለሙያ የሚሰጥ ህክምናን ተግባራዊ ማድረግ፡፡

የተቅማጥና ትውከት በሽታን መከላከያና መቆጣጠሪያ መንገዶች?

• መፀዳጃ ቤት መገንባትና በአግባቡ መጠቀም
• ምግብን በሚገባ አብስሎ መመገብ
• በውኃ /መድሃኒት/ በውኃ አጋር/ የታከመ ውሃ ለመጠጥ መጠቀም ወይም ውኃ አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠጣት
• እጅን በውኃና በሳሙና /በአመድ በደንብ አጥርቶ መታጠብ
• ከመጸዳጃ ቤት መልስ ምግብ ከማዘጋጀት በፊት ምግብ ከማቅረብ በፊት ምግብ ከመመገብ በፊት ሕጻናትን ካጸዳዱ በኋላ ህጻናትን ጡት ከማጥባት በፊት እንዲሁም በበሽታዉ ለተያዙ ሰዎችን እንክብካቤ ካደረጉ በኃላ እጅን በሚገባ መታጠብ::
ማንኛውም ከቤት የሚወጣ ደረቅ ወይም ፈሳሽ ቆሻሻ አካባቢን ወይንም ውኃን እንዳይበክል በአግባቡ ማስወገድ፡፡
• ምልክቱ የታየበትን ህመምተኛ ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋም በመምጣት ማሳከም

• ይህንን መሰረት በማድረግ ሁሉም ህብረተሰብ በሽታዉን በመከላከል ዙሪያ የተሰጡ መልእክቶችን በመተግበር እያንዳንዱ ግለሰብ እራሱንና ቤተሰቡን እንዲሁም አካባቢዉን ሊከላከል ይገባል፡፡

Leave a Reply