August 31 2020, የቶንሲል ህመም
በዶክተር መሐመድ በሽር (የህፃናት ሐኪም)
መግቢያ
👉 በአዳጊ አገራት እድሜያቸው ከ 5 እስከ 15 ባሉ ልጆች ላይ የሚከሰተው የልብ በሽታ (ሪውማቲክ ኸርት ዲዚዝ) ባግባቡ ካልታከመ የቶንሲል ኢንፌክሽን እንደሚከሰት ያውቃሉ? የቶንሲል መርፌ ቀርቷል የሚባሉ ብዝታዎችን ለማጥራት ይረዳን ዘንዳ ካነበብኩት ጀባ አልኳችሁ።
👉 አባት የ3 አመት ልጅ አምጥተው ለልጁ ትኩሳት ምክንያቱ የቶንሲል ኢንፌክሽን ነው ስንላቸው አዎ በረዶ መጥባት ይወዳል ልጁ አሉኝ።
የቀዘቀዘ ምግብን ወይም መጠጥን አብዝቶ መጠቀም አሊያም በሃይለኛ የፀሐይ ሙቀት በመመታት የቶንሲል ኢንፌክሽን ተብሎ በአብዛኛው ህብረተሰብ ዘንድ የሚታሰበው እውነተኛው የቶንሲል ህመም መነሻ ምክንያት አይደለም::
የቶንሲል ህመም ከእዚህ በእጅጉ የተለየና ተገቢውን ህክምና በወቅቱ ካላገኘም እስከሞት ሊያደርስ የሚችል ጉዳት የሚያስከትል አደገኛ የጤና ችግር መሆኑን ያውቃሉ?
መንስሄው ምንድነው ?
ቅባትነት ያላቸውን ምግቦች በፀሐይ ላይ መመገብ፣ እንደ አይስክሬም ያሉ የቀዘቀዙ ምግቦችን በተለይ ለህፃናት መስጠትና በከባድ ፀሐይ መመታት፤ ከቶንሲል ህመም ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለውና በሽታው በባክቴሪያና በቫይረስ ሳቢያ የሚከሰት የጤና ችግር መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።
በጉሮሮአችን ውስጥ የሚገኙት የቶንሲል እጢዎች በጀርሞች ተጠቅተው ሲቆጡና ሲያብጡ የሚከሰተው ህመም ቶልሲላይተስ ተብሎ ይጠራል፡፡ እነዚህ ቶንሲሎቻችን እንዲቆጡና እንዲያብጡ በማድረግ ህመም እንዲሰማን የሚያደርጉት ባክሬቴሪያና ቫይረሶች ናቸው፡፡ የቶንሲል ህመም (ቶንሲላይተስ) በአብዛኛዎቻችን ዘንድ እጅግ የተለመደና በየጊዜው የሚያጋጥም የህመም አይነት ነው፡፡ አንድ ልጅ በየዓመቱ በአማካይ እስከ ስምንት ጊዜ ያህል በቶንሲል ህመም ሊጠቃ ወይንም ቶንሲላይትስ ሊይዘው ይችላል፡፡
የቶንሲል ህመም መንስኤ የሆነው ቫይረስ ወይንም በባክቴሪያ በተለያየ መንገድ በዋነኛነት በትንፋሽ ወደ ሰውነታችን ገብቶ ቶንሲሎቻችንን ከበከለ በኋላ ባሉት ሁለትኛ ሶስት ቀናት በህመምተኛው ላይ የበሽታው ምልክቶች መታየት ይጀምራሉ፡፡
የቶንሲል ህመም ምልክቶች ምንድናቸው ?
የቶንሲል ህመም በብዛት የሚያጠቃዉ ህፃናትን ሲሆን የሚከተሉትን ምልክቶች ሊያሳይ ይችላል፡፡
• የቶንሲል መቅላትና እብጠት
• የቶንሲል መከርከር
• ምግብ በሚዉጡበት ወቅት ህመም መኖር/ መዋጥ መቸገር
• ትኩሳት
• በአንገት ላይ ያበጡና ህመም ያላቸዉ ዕጢዎች መከሰት
• የድምፅ መቀየር
• መጥፎ የአፍ ሽታ
• የሆድ ህመም( በተለይ በእድሜያቸዉ ትናንሽ ህፃናት ላይ)
• የአንገት ህመም/መጠንከር
• የራስ ምታት ናቸዉ፡፡
በጣም ጨቅላ በሆኑ ህፃናትና የህመማቸዉን ሁኔታ መግለፅ በማይችሉ ህፃናት ላይ
• ሲዉጡ ህመም ስላላቸዉ የምራቅ/ለሃጭ መዝረከርክ
• ምግብ መመገብ እምቢ ማለትና
• ያልተለመደ ድካም የህመሙ ምልክቶች ናቸዉ፡፡
ልጅዎ ቶንሲል ኢንፌክሸን እንደያዘው እንዴት ማወቅ ይችላሉ ?
ህመምተኛው አፉን እንዲከፍት በማድረግ ጉሮሮው በሚታይበት ጊዜ ከምላሱ ኋላ በግራና ቀኝ የጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ እብጠትና ቅላት ይታያል፡፡ እነዚህ የጉሮሮ ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ የሚገኙ የቶንሲል እጢዎች እብጠታቸው አንዳንዴ ከፍተኛ ይሆንና ጉሮሮን ሙሉ በሙሉ ሊዘጉ ይችላሉ፡፡ ባክቴሪያ ወለዱ ቶንሲላይት ከመደበኛው የቶንሲል ህመሞች ምልክቶች በተጨማሪ ከሚኖረው የበሽታው ምልክት መካከል በጉሮሮ ግድግዳዎች ላይ በሚኖረው እብጠት ላይ ነጫጭ አይብ መሰል ነጠብጣቦች /ችፍታዎች/ ሊታዩበት ይችላሉ፡፡ የቶንሲል ህመም በትንፋሽ አማካይነት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍና ህፃናትን በይበልጥ የሚያጠቃ የበሽታ ዓይነት ነው፡
የቶንሲል ህመም (ቶንሲላይትስ) በሸታውን በወቅቱ ወይም በዘጠኝ ቀናት ውስጥ አለመታከም አደጋው ምንድነው ?
ስትሬፕቶኮከስ ፓዪጂንስ በተባለው ባክቴሪያ ሳቢያ በሚመጣው የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው በአግባቡና በወቅቱ ህክምናውን ካላገኘ ከኩላሊት መድከም (ኩላሊት ሙሉ በሙሉ ሥራ ማቆም) እስከ ልብ ህመም ብሎም እስከሞት ሊያደርሱ የሚችሉ መዘዞችን ያስከትላል፡፡
በባክቴሪያ ወለዱ የቶንሲል ህመም የተያዘ ሰው ተገቢውን ህክምና ካላገኘ ቶንሲሎቹ ዙሪያቸውን ያብጡና መግል ይቋጥራሉ፡፡ የህመምተኛው አንገትም ይበልጥ መግል ወደተቋጠረበት አቅጣጫ ያዘማል፡፡ ይህም የማጅራት አለመታዘዝንና መንጋጋን እንደልብ መክፈት አለመቻልን ከማስከተሉም በላይ ታማሚው ህክምና ካላገኘ ባክቴሪያው በደም ውስጥ በመሰራጨት የኩላሊትና የልብን መደበኛ ስራ በማስተጓጎል ታማሚውን ለሞት ሊዳርገው ይችላል።ባክቴሪያ አመጣሹ ቶንሲላይተስ ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል አጣዳፊ የኩላሊት መድከም፣ የልብ ህመም፣ የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) የቆዳና የጉሮሮ ኢንፌክሽኖች፣ ጥቂቶቹ ናቸው።
ስትሬፕቶከክስ ፓዮዲኒስ በተባለው የባክቴሪያ አይነት ሳቢያ የሚከሰተውን እና እጅግ አደገኛ የሆኑ ችግሮችን የሚያስከትለውን የቶንሲል አይነት ቫይረስ አመጣሽ ከሆነውና በቀላሉ ከሚድነው የቶንሲል አይነት መለየቱ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም ሁሉም ዓይነት የቶንሲል ህመሞች በአግባቡና በወቅቱ ህክምና ማግኘት አለባቸው፤ የሚባለውም ለዚሁ ነው።
የህክምና ባለሙያ ማማከር የሚገባዎ መቼ ነዉ?
• በ24 ሰዓታት ዉስጥ ለዉጥ የሌለዉ የቶንሲል ህመም ካጋጠመዎ
• ምግብ ሲዉጡ ህመም ካለዎና
• የድካም/የመዝለፍልፍ ስሜቶች ከፍ ያለ ከሆኑ የህክምና ባለሙያዎን ማማከር ያስፈልጋል፡፡
ለቶንሲል ህመም የሚያጋልጡ ነገሮች
• ለጋ እድሜ፡- የቶንሲል ህመም ትናንሽ ህፃናትንና ለጋ እድሜ ላይ ያሉ ልጆችን በብዛት ያጠቃል፡፡
• በተደጋጋሚ ኢንፌክሽኑን ለሚያመጡ ጀርሞች መጋለጥ፡- በትምህርት ቤት የሚዉሉ ህፃናት ከአቻዎቻቸዉ ጋር ያላቸዉ የቀረበ ግንኙነት/ንክኪ ለቫይረሶችና ባክቴሪያዎች በቀላሉ እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል፡፡
የቶንሲል ህክምና ምንድናቸው ?
1. የቤት ዉስጥ ህክምና
የቶንሲል ህመሙ በቫይረስም ይሁን በባክቴሪያ ምክንያት ቢከሰትም የቤት ዉስጥ ህክምናዎችን መከወን ምቾት እንዲሰማዎና ቶንሲሉ ቶሎ እንዲድን ያደርገዋል፡፡ የቶንሲል ህመሙ የተከሰተዉ በቫይረስ መሆኑ ከተረጋገጠ የህክምና ባለሙያዎ ምንም ፀረ ባክቴሪያ መድሃኒት ስለማያዝልዎ ህመሙ እንዲድን የቤት ዉስጥ ህክምና ማከናወን የህክምናዉ ዋናዉ አካል ነዉ፡፡ የቶንሲል ህመም በ10 ቀናት ዉስጥ ሊሻሻል ይችላል፡፡
ሊደረጉ የሚችሉ የቤት ዉስጥ ህክምናዎች
• በቂ እረፍት ማግኘት፡- ብዙ ያለማዉራትና በቂ እንቅልፍ ማግኘት
• ፈሳሽ በበቂ መጠን መዉሰድ
• ምቾትን ሊሰጡ የሚችሉ ምግቦችን መመገብ፡- ትኩስ ፈሳሾች እንደ ሾርባ፣ካፊን የሌለዉ ሻይ፣ የሞቀ ዉሃ በማር እንዲሁም ቀዝቃዛ የሆኑ እንደ በረዶ ያሉ ነገሮች የጉሮሮ መከርከርን ሊያክሙ ይችላሉ፡፡
• ጨዉ ባለዉ ዉሃ አፍን መጉመጥመጥ
• ወደ ዉስጥ የሚገባዉን አየር እርጥበታማ/ሂሙድፋይ እንዲሆን ማድረግ፡- ወይ የቀዝቃዛ አየር ሂሙድፋየር መጠቀም አለዚያ ደግሞ እንፋሎት መታጠን ደረቅ አየር ጉሮሮ ላይ የሚያመጣዉን መከንከን እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡
• ሊቆጠቁጡ የሚችሉ ነገሮችን ማስወገድ፡- ጉሮሮን ሊከረክሩ ከሚችሉ እንደ የሲጋራ ጭስና የቤት ማጽጃ ኬሚካሎች እራስን መጠበቅ
• ህመምና ትኩሳት ካለ ማስታገሻ መዉሰድ፡- እንደ ፓራሲታሞላና አይቡ ፕሮፌን ያሉ መድሃኒቶችን መጠቀም፡፡
2. መድሃኒቶች
የቶንሲል ህመም የተከሰተዉ በባክቴሪያ ኢንፌክሽን ከሆነ የግድ ፀረ-ባክቴሪያ መድሃኒቶችን (አንቲባዮቲክሶችን) መዉሰድ ያስፈልጋል፡፡
.
ከአስር ቀናት ሹርፕ አለርጅ ለሌላቸው አንድ ጊዜ የሚሰጠው መርፌ ይመከራል።በህክምና ባለሙያዎ የታዘዘልዎትን መድሃኒት በአግባቡ ወስዶ መጨረስ የሚያስፈልግ ሲሆን በአግባቡ ካልተወሰደ ግን ባክቴሪያዉ ወደ ሌላ ቦታ እንዲሰራጭ፤ህፃናት ላይ ደግሞ የልብ ህመም እንዲከሰት መንስኤ መሆንና ቀጣይነት ያለዉ የቶንሲል ህመም (ክሮኒክ ቶንሲላይትስ) እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
የቶንሲል ህመምን እንዴት መከላከል ይቻላል ?
ቶንሲልን ሊያመጡ የሚችሉ ጀርሞች (ባክቴሪያና ቫይረስ) ከሰዉ ወደ ሰዉ ተላላፊ ናቸዉ፡፡ ስለሆነም የቶንሲል ህመምን ለመከላከል ከሚረዱ መንገዶች ዉስጥ ዋነኛዉ የግል ንፅህናን መጠበቅ ነዉ፡፡ እራስዎም ሆኑ ልጆችዎ
• ምግብ ከመመገባችሁ በፊትና ከመፀዳጃ ቤት መልስ እጃችሁን በደንብ መታጠብ
• የመጠጫና መመገቢያ እቃዎችን በጋራ ያለመጠቀም ይመከራል፡፡
ልጆች የቶንሲል ህመም ካላቸዉ ኢንፌክሽኑን ወደሌሎች እንዳያዛምቱ
• ልጅዎ ታሞ ከሆነ ለተወሰነ ቀናት እቤት እንዲቆይ ማድረግ
• ልጅዎ መቼ ት/ት ቤት መሄድ እንደሚችል የህክምና ባለሙያዎን ማማከር
• ልጅዎ በሚስልበትና በሚያስነጥስበት ወቅት አፍና አፍንጫዉን በሶፍት ወይም በክርኑ የዉስጠኛዉ ክፍል እንዲሸፍን ማስተማርና
• ልጅዎ ካሳለዉ ወይም ካስነጠሰዉ በኃላ እጁን/እጇን እንዲታጠቡ ማስተማር ናቸዉ፡፡
©Hakim
[email-subscribers-form id=”1″]
For More Health related Articles Click Here
To Get alerts of our latest healthcare articles Go-to Our Telegram channel