August 29 2020
ከዚህ ቀደም የተሠሩ ጥናቶች ፤ ኮሮናቫይረስ (ሳርስ-ኮቭ 2) የተገኘባቸው አብዛኛዎቹ ልጆች ከመጠነኛ ምልክት እስከ ምንም ምልክት እንደማያሳዩ ይጠቁማሉ።
እነዚህ ግኝቶች ልጆች ምን ያህል በሽታውን ያሰራጫሉ ለሚለው እስካሁን በቂ ምላሽ ላልተገኘለት ጥያቄ ፍንጭን ይሰጣሉ ።
ለወራት እንቅስቃሴ አቁመው በነበሩ አገሮች በአሁኑ ሰአት ትምህርት ቤቶች እየተከፈቱ ቢሆንም አካላዊ ርቀትና ንጽህናን መጠበቅ መዘንጋት እንደሌለበት ተመራማሪዎች ይናገራሉ::
የተመራማሪዎቹን ምክር የሚያጠናክር በደቡብ ኮርያ የተሠራ አንድ ተጨማሪ ጥናት ልጆች ኮሮናቫይረስን (ሳርስ-ኮቭ 2ን) በአፍንጫቸው ላይ ይዘው እስከ ሦስት ሳምንታት መቆየት እንደሚችሉ አሳይቷል።
የደቡብ ኮርያው ጥናት የተሠራው 91 ልጆች ላይ ሲሆን መጠነኛ ወይም ምንም ምልክት የማያሳዩ ልጆች አፍንጫ ላይ ቫይረሱ እስከ ሦስት ሳምንት ድረስ እንደሚቆይ ከልጆቹ በተወሰደ ናሙና መረዳት ተችሏል።
በልጆቹ አፍንጫ ላይ የቫይረሱ ምልክት መገኘቱ፤ ልጆች በሽታውን ወደ ሌላ ሰው ማስተላልፍ እንደሚችሉ እንደሚጠቁም የጥናቱ ጸሐፊዎች አስረድተዋል።
ጥናቱ ልጆች ቫይረሱን እንደሚሸከሙ እና፣ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊያስተላልፉ እንደሚችሉም ጠቁሟል።
ሆኖም ግን ጥናቱ ለሁሉም ጥያቄዎች መልስ አልሰጠም።
ልጆች አፍንጫ ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል ማለት የአዋቂዎች ያህል ቫይረሱን ያስተላልፋሉ ማለት አይደለም።
በሕፃናት ሕክምና ክፍል የሚሠሩት ዶ/ር ሮበርታ ዲባሲ ልጆች ቫይረሱን ሊያስተላልፉ አይችሉም ማለት እንደማይቻል ያስረዳሉ።
የቫይረሱ ዘረ መል ከመተንፈሻ አካላት በሚወሰድ ናሙና ላይ መገኘቱ በሽታውን ከማስተላለፍ ጋር የግድ እንደማይተሳሰር የሚናገሩት ደግሞ የሊቨርፑል ዩኒቨርስቲ ፕ/ር ካሉም ሰምፕል ናቸው።
ልጆችም ይሁን አዋቂዎች መጠነኛ ወይም ምንም አይነት ምልክት ካላሳዩ በሽታውን የማስተላለፍ እድላቸው አናሳ መሆኑን ጥናቶች ያሳያሉ።
የማያስሉ ወይም የማያስነጥሱ ሰዎች ቫይረሱን ወደ አየር እምብዛም አይለቁም።
ሆኖም ግን ምልክት የማያሳዩ ሰዎች በሽታውን አያሰራጩም ማለት አይደለም።
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ አብዛኞቹ ልጆች በተወሰነ ደረጃ ወይም ሊታይ በማይችል ሁኔታ ነው በቫይረሱ ሊያዙ የሚችሉት። በማኅበረሰቡ ውስጥ ቫይረሱን ሊያሰራጩ ግን ይችላሉ።
#BBC