You are currently viewing የኮቪድ-19 ጠንቆች (Complications) ‼️

የኮቪድ-19 ጠንቆች (Complications) ‼️

August 20 2020

እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የጤና ባለሞያዎችን ምክር ችላ በማለት ይህን ዘመን አመጣሽ በሽታ( ኮቪድ-19ን) እንደተራ የጉንፋን ወረርሽኝ የቆጠሩ ብዙዎች ነበሩ:: ባለፉት ጥቂት ወራት የተጠኑ ጥናቶች ግን ይህ አለም ከዚህ በፊት በማያውቀው አዲስ የኮሮናቫይረስ ሚያመጣቸው ጠንቆች ላይ ጭልጭል የምትል ብርሀን አብርተውበታል::

አንድ ነገር እርግጥ ነው ይህ ቫይረስ አዲስ እንደመሆኑ መጠን ገና ስለሱ ወደፊት ብዙ እንማራለን:: አሁን ግን ሳይንስ በጥናት ከደረሰባቸው የኮቪድ-19 ጠንቆች መካከል ጥቂቶቹን እንመልከት::

1. በአእምሮ ላይ
2. በልብ ላይ
3. በሳንባ ላይ
4. በኩላሊት ላይ

1. በአእምሮ ላይ

ኮቪድ-19 ከያዛቸው ሰዎች 55 በመቶ የሚሆኑት ከነርቭ ስርአት መዛባት ጋር የተገናኙ ምልክቶች ይኖራቸዋል::
እነዚህ ምልክቶች አንድ ሰው ከቫይረሱ ካገገመ በኋላ የሚጀምሩ ሲሆኑ ትኩረትን ለመሰብሰብ መቸገር ፣ ግራ መጋባት እራስምታት፣ ድካም፣ የስሜት መቀያየር፣ እንቅልፍ ለመተኛት መቸገር፣ መቅመስና ማሽተት አለመቻል ይገኙበታል::

ጥናቱ የተካሄደው የኮቪድ-19 ታማሚዎች የነበሩ 60 ግለሰቦችን ከቫይረሱ ካገገሙ በኋላ ለወራት በመከታተል ነበር:: ይህ ጥናት እንዳሳየው ከእነዚህ ሰዎች 55 በመቶ የሚሆኑት እስከ 3 ወር ክትትል ድረስ ከላይ የተጠቀሱት ምልክቶች እንደነበሯቸው ማረጋገጥ ተችሏል::

ሌሎች ጥናቶች እንዳገኙት ደግሞ ኮቪድ-19 ለስትሮክ፣ ቅዠት እና ለጭንቀትም ሊዳርግ ይችላል::

ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የተረጋገጡ በርካታ ሰዎች በመጀመሪያ አካባቢ ብዙም የሚሰጋ ህመም የማይሰማቸው ሲሆን፤ ቀስ በቀስ ግን ማስታወስ አለመቻልና ድካምን የመሳሰሉ ጠንከር ያሉ ምልክቶች ማሳየት ይጀምራሉ።
የ64 ዓመቱ ፖል በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የኮምዩኒኬሽንስ ኃላፊ ሲሆን እምብዛም ስጋት ውስጥ ሊከተው ሚችል የጤና እክል አልነበረበትም። በለንደኑ የአንጎልና የአንጎል ቀዶ ህክምና ብሔራዊ ሆስፒታል ውስጥ እጅግ ከፍተኛ የጤና መሻሻል ያሳየ የኮሮረናቫይረስ (ሳርስ-ኮቭ2) ታማሚ ሆኗል። ካጋጠመው ስትሮክ በኋላም ፖል ጥሩ የሚባል መሻሻል ታይቶበታል።

የመጀመሪያው ስትሮክ ያጋጠመው በሆስፒታል የጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ እያለ ነበር። በዚህ ምክንያት ሕይወቱ ልታልፍበት የምትችለበት እድልም ከፍተኛ ነበር። ለዚህም ሲባል ደም የሚያቀጥን መድኃኒት እንዲወስድ ተደርጎ ነበር።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ስትሮክ አጋጠመው። ሁለተኛው ግን በጣም የከፋና ሕይወቱን ትልቅ አደጋ ውስጥ የከተተ ነበር።

አማካሪ የአንጎል ሐኪም ሆኑት ዶክተር አርቪንድ ቻንድራቴቫ፤ ፖል በአምቡላንስ ወደ ሆስፒታሉ ሲመጣ ሥራቸውን ጨርሰው እየወጡ ነበር። ”ፖል ፊቱ ላይ ግራ መጋባት ይስተዋልበት ነበር። መመልከት የሚችለው በአንድ አቅጣጫ በኩል ብቻ ነበር፤ ተንቀሳቃሽ ስልኩን ለመጠቀምም ሲቸገርና የይለፍ ቃሉን ማስታወስ አቅቶት ግራ ሲጋባ ነበር” ብለዋል ዶክተሩ።

ዶክተር አርቪንድ እንደሚሉት በፖል ጭንቅላት ውስጥ አጋጥሞ የነበረው የደም መርጋት ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት አይነት እንደሆነ ይናገራሉ።

ፖል በተደረገለት ምርመራ የደም መርጋት ምልክቶች ታይተውበታል። በምርመራው የተገኘው ውጤትም አጋትሟቸው በማያውቁት ሁኔታ እጅግ የተለየና አሳሳቢ ነበር።

“በሕይወቴ እንዲህ ያለ ውስብስብና ከፍተኛ ከፍተኛ ደም መርጋት ሁኔታ ተመልክቼ አላውቅም” የሚሉት ዶክተር አርቪንድ ኮሮናቫይረስ(ሳርስ-ኮቭ2) የፖል ደም በእጅጉ የተጣበቀ እንዲሆን እንዳደረግ ይገልጻሉ።

2. በልብ ላይ

ከኮቪድ-19 ካገገሙ ታማሚዎች ሶስት አራተኛዎቹ ካገገሙ በወራት ጊዜ ውስጥ የልብ መጎዳት እንደሚኖራቸው አንድ ጥናት አመልክቷል::

ሰኞ እለት በጃማ ካርዲዮሎጂ ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንዳሳየው ከኮቪድ 19 ካገገሙ ታማሚዎች በልባቸው ላይ የገፅታ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል አሳይቷል::

በአንድ መቶ እድሜያቸው ከ45-53 የሚሆኑ ከኮቪድ 19 ያገገሙ ታካሚዎች ላይ የተሰራው የ ኤም.አር.አይ ምርመራ የተወዳደረው በቫይረሱ ተይዘው ከማያውቁ ሰዎች ኤም.አር.አይ ጋር ነበር::

ከመቶዎቹ ሰዎች 53ቱ ቤታቸው ራሳቸውን ሲያስታሙ የነበሩ ሲሆን 33ቱ ደግሞ በቫይረሱ ከተያዙ በኋላ ሆስፒታል የገቡ ናቸው::

ከነዚህ መቶ ታካሚዎች ውስጥ 78ቱ በልባቸው ላይ የገፅታ ለውጥ የታየ ሲሆን ከነዚህም 76ቱ ትሮፖኒን ቲ የተሰኘ ኸርት አታክ( Heart Attack) ያጋጠማቸው ሰዎች ላይ የሚታየው ኬሚካል መጠን በደማቸው ውስጥ ከፍ ብሎ መገኘቱ ታውቋል::

ከመቶ 60ዎቹ ደግሞ ማዮካርዳይቲስ የተሰኘ የልብ በሽታ ተገኝቶባቸዋል:: በሽተኞቹ በአንፃራዊነት በኮቪድ-19 ከመያዛቸው በፊት ጤነኛ የነበሩ ናቸው::
3. በሳንባ ላይ

የሰው ልጅ ሳንባ በአማካይ 500 ሚለየን የሚሆኑ ትናንሽ አየር መሳቢያ ፊኛ (alveoli) አሉት :: የነዚህ ፊኛዎች ጤና የምንስበውን የአየር ብሎም የምናገኘውን ኦክስጂን መጠን (gas exchange) ይወስነዋል:: አየር ወደ ውስጥ ስንስብ እኚህ ፊኛዎች እስከሚለጠጡ ይሞላሉ፡፡ ከነዚሀ ፊኛዎች ጀርባ የሚገኝ ቀጭን የደም ስር (perialveolar capillary) የአየር ፊኛዎቹ ሲሞሉ (ሲለጠጡ) በግድግዳቸው ላይ አምልጦ (diffusion) የሚተንለትን አክሲጅን ተቀብሎ ወደ ሰውነት ይገባል… እግረ መንገዱንም የያዘውን የተቃጠለ ጋዝ (CO2) ወደ አየር ፊኛ ያተናል፡፡ በዚህ ሒደት አክሲጂን አገኘን ህይወትም ቀጠለች ማለት ነው፡፡

በሰው ልጅ ተፈጥሮ በአየር ፊኛ (alveoli) እና ኦክሲጂን ተቀብሎ በሚወስደው የደም ስር (Capillary) መካከል ያለው ግድግዳ እጅግ እጅግ ሲበዛ ቀጭን ነው፡፡ ኦክስጂን ወደ ሰውነት መግባትም ሆነ ጒጂ የሆነ ጋዝ መውጣት (gas exchange) ሊካሔድ የሚችለው ቅጥነቱ እንደተጠበቀ ከኖረ ብቻ ነው። ከወፈረ እንደ መታነቅ ቁጠሩት!

የኮቪድ-19 በሽታ ሲከፋ ( Severe form) ይህ ወሳኝ አካባቢ በሰውነት መከላከያ ይደበደባል። በጥቃቱም የአየር ፊኛውም ሆነ የደም ስሩ ግድግዳ ይቆስላል(Collateral damage) ፡፡ የአየር ፊኛው ጀርባ ያለው የደም ስሩ ግድግዳ ስለሚቀደድ በደምስሩ ውስጥ የነበረው ፈሳሽ እና ፕሮቲን (plasma protein) ደምስሩን ለቆ ይፈሳል… የአየር ፊኛው በፈሳሽ ይጥለቀለቃል (proteinaceous excudates in alveolar space) :: አካባቢው በፈሳሽ, በሞቱ ወታደሮች እና በቆሻሻ ይሞላል፡፡ የፈነዳውን የአየር ፊኛም ለመድፈን በሚደረገው የጥገና ስራ በጠባሳ ይሞላል (pneumocyte hyperplasia)፡፡ ጠባሳው ወፍራም ስለሚሆን ቀዳዳው ቢጠገንም ግድግዳዉ ኦክስጅን አያሳለፍም ወይም በቀላል ቋንቋ ስስ የነበረው ፊኛ የዘይት ጀሪካን ሆነ ማለት ነው። አይለጠጥም…. አየር ብንስብበት እንኳ አክሲጂን አያሳልፍም …ዋጋ የለውም፡፡ በዚህም አየር ማስተላለፍ ኖሮበት የማያስተላልፍ ሰነፍ ክፍል በሳንባችን ይጨምራል (rise in physiologic dead space)፡፡ የዚሀ አይነት ሳንባ ክፍል እንደሞተ ይቆጠራል። ሰውነት እና የአየር ፊኛው .እንደተለያዩ ይቀራሉ!

ሰውየው ከኮቪድ-19 ካገገመ የተረፈ ቢመስልም ካሉት 500 ሚሊየን አየር መሳቢያ ፊኛ (alveoli) ውስጥ ምናልባት 300 ሚለየን ገብሮ ሞተውበት ሊሆን ይችላል …ቀሪ ህይወቱን በ200 ሚለየን ፊኛ ይጋፈጣል እንደማለት ነው። በሌላ ቋንቋ ስድስት ሲለንደር መኪናን ባለ ሁለት ቢደረግ ችግሩ ምን ይሆናል ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ…V8 ወደ ላዳነት ቢቀየር ለውጡ የሚታወቀው ዳገት ላይ ሊሆን ይችላል …መዳኑ ያለ ኪሳራ አይደለም፡፡ የእድሜ ልክ ችግር ጥሎ የሚሔድ በሽታ ነው።
4. ኩላሊት ላይ

እንደ አሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ገለፃ በኮቪድ-19 የተያዙ አንዳንድ ሰዎች የኩላሊት ጉዳት ያጋጥማቸዋል::ይህ ጉዳት የሚፈጠረው ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የኩላሊት በሽታ ባልነበራቸው ሰዎች ላይ ጭምር ነው:: በቻይና እና በአሜሪካ ኒውዮርክ የተጠና አንድ ጥናት እንዳሳየው በኮቪድ-19 ተይዘው ሆስፒታል ከገቡ ሰዎች መሀል 30 በመቶ የሚሆኑት ከመካከለኛ እስከከፋ የኩላሊት መጎዳት አጋጥሟቸዋል::
በኮቪድ-19 በተያዙ ሰዎች ላይ የሚታየው የኩላሊት መጎዳት ከፍተኛ በሽንት ውስጥ ያለ የፕሮቲን መጠን እና በተዛባ የደም ምርመራ ውጤት ይታያል::

በአንዳንድ ታማሚዎች ላይ የሚታየው የኩላሊት መጎዳት የኩላሊት እጥበት(ዲያሊሲስ) ጭምር እንደሚያስፈልገው ዩኒቨርሲቲው በድህረገፁ ላይ አስነብቧል::

ቫይረሱ እስካሁን ኩላሊትን እንዴት እንደሚጎዳ ሙሉ በሙሉ ባይታወቅም ሀኪሞችና ተመራማሪዎች ምክንያት ሊሆኑ የሚችሉ ብዙ መንገዶች ላይ ጥናቶቻቸውን ቀጥለዋል::

ከዚህ ዘመን አመጣሽ ክፉ በሽታ እራሳችንን እንጠብቅ!!

Source:-

https://jamanetwork.com/journals/jamacardiology/fullarticle/2768916

https://www.hopkinsmedicine.org/health/conditions-and-diseases/coronavirus/coronavirus-kidney-damage-caused-by-covid19

 

Leave a Reply