You are currently viewing የኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ ‘የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው’ -በአሜሪካ የተደረገ ጥናት

የኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ ‘የመተላለፍ ዕድሉ ዝቅተኛ ነው’ -በአሜሪካ የተደረገ ጥናት

 

የኮሮናቫይረስ ላለባቸው እናቶች አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ከተደረገ በወሊድ ጊዜ ወደ ህጻናቱ የመተላለፍ እድሉ ዝቅተኛ ሊሆን እንደሚችል አንድ ጥናት አመለከተ።

አሜሪካ ኒው ዮርክ ውስጥ በሚገኙ ሦስት ሆስፒታሎች ኮሮናቫይረስ ካለባቸው እናቶች ከተወለዱ 120 ህጻናት ውስጥ አንዳቸውም በበሽታው አለመያዛቸው ተረጋግጧል።

ይህ ውጤት የተገኘው ህጻናቱ ከተወለዱ በኋላ ባለው ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከተወለዱ ከሁለት ሳምንታት በኋላ አንዳንዶቹ የእናታቸውን ጡት የመጥባት እድል ካገኙና በአንድ ክፍል ውስጥ አብረው ከቆዩ በኋላም ጭምር ነው።

ጥናቱን ያደረጉት ባለሙያዎች እንደሚሉት የተገኘው ውጤት ተስፋ ሰጪ ቢሆንም #ተጨማሪ_ሰፋ_ያሉ_ሙከራዎች ማድረግ ያስፈልጋል።

በእርግዝናና በጡት ማጥባት ወቅት የበሽታውን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ሁኔታን በተመለከተ ያለው መረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የሚሰጠው ምክርም የተለያየ እንዲሆን አድርጎታል።

የዩናይትድ ኪንግደም ሐኪሞች እናቶች ጡት ማጥባት የሚፈልጉ ከሆነ አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ ተደርጎላቸው ልጆቻቸውን ጡት ማጥባትም ሆነ አንድ ክፍል ውስጥ መሆን ይችላሉ ብለዋል።
#WHO
ባለሙያዎቹም ሆነ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚሉት በኮሮናቫይረስ የመያዝ ስጋት የበለጠ ጡት ማጥባት ያለው ጠቀሜታ የጎላ ነው።
#CDC
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል የቫይረሱን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ዕድልን ለመቀነስ አዲስ የተወለዱ ህጻናት ለተወሰነ ጊዜ ከእናታቸው ተለይተው እንዲቆዩ የማድረግ ሃሳብን ተግባራዊ ለማድረግ እያሰበ ነው።
_______
ኮሮናቫይረስ ያለባት እናት ከወለደችው ልጅ ጋር በአንድ ክፍል ውስጥ እንድትቆይ የሚደረግና ጡት እንድታጠባ የሚፈቀድላት ከሆነ፤ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል እንድትጠቀምና በተደጋጋሚ እጇን መታጠብ እንደሚኖርባት በጥናቱ ተመልክቷል።

ጥናቱን የመሩት ዶክተር ክርስቲን ሳልቫቶሬ እንዳሉት “ጥናታችን ወረርሽኙ ያለባቸው እመጫት እናቶች ቫይረሱን ወደ ልጃቸው የማስተላለፍ ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው። ነገር ግን ሁኔታውን የበለጠ ለመረዳት አሁንም ሰፋ ያለ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል” ብለዋል።

በጉዳዩ ላይ በዩናይትድ ኪንግደም የተደረገ ቅኝትን የመሩት ፕሮፌሰር ማሪያን ናይት እንደገለጹት ጥናቱ በአገሪቱ ያለውን መመሪያ የሚደግፍና የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።

ጨምረውም “በዩናይትድ ኪንግደም ከአንድ ሺህ በላይ ኮቪድ-19 ያለባቸው እናቶች የወለዱ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ከ1 እስከ 2 በመቶ የሚሆኑት ህጻናት ላይ ብቻ ነው ቫይረሱ የተገኘው። በሽታውም በህጻናቱ ላይ የከፋ ህመምን አላስከተለም።”

በአሜሪካ የተደረገው አነስ ያለ ጥናትም የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምበል መጠቀመን የመሰሉ ቀላል የጥንቃቄ እርምጃ በመውሰድ የኮሮናቫይረስ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ሁኔታ እንዳይከሰት ማድረግ መቻሉን ፕሮፌሰሯ ጠቅሰዋል።

የጥናቱ ውጤት የህጻናትና የአዋቂዎች ጤና ጉዳይ ላይ በሚያተኩረው የላንሴት የህክምና ሙያዊ መጽሔት ላይ ታትሟል።

#BBC

Leave a Reply