You are currently viewing ሰው ለምን ራሰ በራ ይሆናል? -የጥያቄዎቻችሁ መልስ #7

ሰው ለምን ራሰ በራ ይሆናል? -የጥያቄዎቻችሁ መልስ #7

ጠያቂ:- ወጣት ወንድ
ጥያቄ:- ሰው ለምን ራሰ በራ ይሆናል?

የእኛ መልስ
ራሰ በራነት ምንድን ነው? መነሻው እና ህክምናው ምንድን ነው?

ፀጉር በማንኛውም የሰውነታችን ቆዳ ላይ ከእጃችን መዳፍ እና ከእግራችን ሶል ዉጪ ይበቅላል ነገር ግን አብዛኛዎቹ ፀጉሮች ስስ ስለሆኑ በአይናችን ላናያቸው እንችላለን፡፡ ፀጉር ኬራቲን(keratin) ከሚባለው ፕሮቲን በዉጨኛው የቆዳ ክፍል የፀጉር ፎሊክል ዉስጥ ይሰራል፡፡

ፎሊክላችን አዲስ የፀጉር ሴል ሲሰራ/ሲያመርት አሮጌ ሴሎቻችን በአመት 6 ኢንች ወደ ዉጪ ቆዳችን ተገፍተው ይወጣሉ የምናየው ፀጉር የሞተ ክር መሳይ ኬራቲን ሴል ነው፡፡ በአማካይ የአንድ አዋቂ ሰው ጭንቅላት ከ 100,000-150,000 የሚደርስ ፀጉር ሲይዝ በቀን 100 ፍሬ ፀጉር በራሳቸው ጊዜ ይነቀላሉ በማበጠሪያች ውስጥ ትንሽ የተነቀሉ ፀጉር ማግኝት የተለመደ እና ሊያስደነግጠን የማይገባ ጤናማ ሁኔታ ነው፡፡

ፀጉር እምራች የሆኑት እያንዳንዳቸው ፎሊክሎች የራሳቸው የሆነ የእድሜ ገደብ ሲኖራቸው በእድሜ፣ በበሽታ እና በተለያዩ በርካታ ምክንያቶች ተጽእኖ ይወሰናሉ፡፡ ይህ አውደ ህይወት በሶስት የለውጥ ደረጃ ይከፈላሉ

1. አናጅን ፦ ፀጉር በፍጥነት የሚያድግበት ጊዜ ሲሆን ከ2-6 ዓመት ያበቃል
2. ካታጂን፦ ይህ የፀጉር እድገት ጊዜ የሽግግር ደረጃ ሲሆን ከ2-3 ሳምንት ይፈጃል
3. ቴሎጂን፦ የእድገት ጊዜ የሚያርፍበት/የሚቆምበት ሲሆን ከ2-3 ወር ይፈጃል፡፡

በዚህ የለውጥ ደረጃ መጨረሻ ላይ ፀጉራችን ይረግፍና የዕድገት ሂደቱን እንደገና ከመጀመሪያ ይጀምራል፡፡

እድሜያችን እየጨመረ ሲሄድ የፀጉር እድገት ፍጥነቱን ይቀንሳል፡፡ ፀጉራችንን የምናጣበት በርካታ ዓይነቶች አሉ እነሱም

አንድሮጀኒክ አሎፔሺያ

ወንድና ሴትን የሚያጠቃ በዘር ህዋስ ምክንያት የሚከሰት ነው፡፡ ወንዶች በወጣትነታቸው ወይም በሃያዎቹ መጀመሪያ ፀጉራቸው ያሳሳል፡፡ በመሃልና በፊት ጭንቅላታቸው ላይ ያሉ ፀጉሮች ቀስ በቀስ ያሳሳሉ፡፡ ሴቶች እድሜያቸው 40 እስከሚሆን የፀጉር መሳሳት አይታይባቸውም፡፡ ሴቶች አጠቃላይ በጭንቅላታቸው ላይ ያለ ፀጉር ይሳሳል በተለይ መሀል አካባቢ፡፡

አሎፔሺያ አርያታ

በድንገት የሚጀምር ሲሆን በመጠንም ሆነ በአይነት ያልተስተካከለ ፀጉርን ማጣት በህፃናት እና ወጣቶች ላይ ያጋጥማል፡፡ ሙሉ ለሙሉ የፀጉር መመለጥ ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ከተጠቁት 90 የሚሆኑት ሰዎች በጥቂት አመታት ውስጥ ፀጉራቸው ተመልሶ ይበቅላል፡፡

አሎፔሺያ ዩኒቨርሳሊስ

ሁሉም የሰውነታችን ክፍሎች ፀጉር ቅንድብ፣ የአይን ሽፋሽፍትና የሀፍረተ ስጋ አካባቢ ፀጉሮች ሙሉ ለሙሉ ይረግፋሉ፡፡

ስካሪንግ አሎፔሺያ

በቋሚነት የፀጉር መርገፍ ሲሆን በተለያዩ የቆዳ ችግሮች ይከሰታል፡፡

መነሻ ምክንያቶች

የተለያዩ ብዙ ምክንያቶች ፀጉራችን እንዲረግፍ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ከነዚህም መካከል

ሆርሞን

የተዛባ የአንድሮጂን ሆርሞን መጠን (የወንድ ሆርሞን ሲሆን በወንድና ሴቶች ይመረታል)

ጂን(ዘረ መል)

ከሁለቱም ወንድ እና ሴት ወላጆች ለወንድ ወይም ሴት ልጅ መመለጥ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡

ጭንቀት፣ ህመም እና ወሊድ

ጊዜያዊ የሆነ የፀጉር መርገፍ ያስከትላል፡፡ የሆድ ትላትሎችና የፈንገስ ኢንፊክሽን ተጠቃሽ ናቸው

መድሃኒቶች

ለካንሰር ህክምና የሚዉለው ኬሞቴራፒ፣ የደም መቅጠን፣ ለደም ግፊት የሚዉሉ መድሃኒቶች፣ አንዳንድ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎች ጊዜያዊ የሆነ የፀጉር መርገፍ ሊዳርጉን ያችላሉ፡፡

ቃጠሎ፣ አደጋና ራጅ

ጠባሳ እስካልተከሰተ ድረስ አደጋው በሚድንበት ጊዜ መደበኛ ፀጉራችን መብቀል ይጀምራል፡፡

የኮስሞቲክስ ውጤቶች

በብዛት ሻምፖ፣ ፐርም እና የተለያዩ ንጽህና መጠበቂያዎች ፀጉር በቀላሉ እንዲሰበር በማድረግ ለፀጉር መሳሳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ለራሰ በራነት ላይዳርጉን ይችላሉ፡፡

የጤና ችግሮች

የታይሮይድ በሽታ፣ የስኳር በሽታ፣ የብረት እጥረት፣ የአመጋገብ ችግርና የደም ማነስ የፀጉር መመለጥ እንዲከሰት ያደርጋሉ

ምግብ

የፕሮቲን መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦችና የካሎሪ መጠናቸው ዝቅተኛ የሆኑ ምግቦች የፀጉር መመለጥ እንዲከሰት ያደርጋሉ፡፡

የራሰ በራነት ህክምና
~~~
ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መድሃኒቶች በህክምና የተረጋገጡ በተሳካ ሁኔታ የራሰ በራነትን ይከላከላሉ ተብሎ ይታመንባቸዋል

ሚኖክሲዲል(ሮጌይን)

ያለ ምንም መድሃኒት ማዘዣ ልንገዛው የምንችል መድሃኒት ሲሆን ሴቶችም ሆነ ወንዶች ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ በተለይ በመሃል አናት ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ይሰራል በፊት ለፊት የፀጉራችን ክፍል ላይ የመስራት እድላቸው ዝቅተኛ ነው፡፡ በ2%፣ 4% የተዘጋጀ ሲሆን በከባድ መጠን 5% ተዘጋጅተዋል፡፡

ይህ መድሃኒት ትንሽ አዲስ ፀጉር ሊያበቅል ይችላል ዋናው ጥቅሙ ግን ፀጉራችን ባለበት ቦታ ላይ እንዲቆም(እንዳይመለጥ) ይረዳል፡፡ የዚህ መድሃኒት ችግር በቀን አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ስለምንጠቀመው ሊያሰለቸን ይችላል፡፡ በአንገት ወይም ፊት ላይ መድሃኒቱ የሚነካን ከሆነ ያልተፈለገ ፀጉር ሊነቅልብን ይችላል፡፡

ፊናስቲራይድ

በአሜሪካ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የተረጋገጠ ሲሆን ለወንዶች ጥቅም ብቻ ይውላል፡፡ ተፈጥሮአዊ የጭንቅላት ፀጉር ፎሊክሎችን ሆርሞን በመዝጋት ፀጉር እንዳይበቅል ያደርጋል፡፡ ፕሮፔሺያ/ በዝቅተኛ መጠን የተዘጋጀ ፕሮስካር/ የተባለ መድሃኒት ዝርያ ነው ይህ መድሃኒት ትልቅ ፕሮስቴቶችን በማጨማደድ በመካከለኛ እና ትልቅ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ወንዶች ይጠቅማል፡፡ ፕሮፔሺያ በ1 ሚ.ግ. የተዘጋጀ በመድሃኒት ማዘዣ በየቀኑ የሚወሰድ መድሃኒት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ፀጉራችንን ለመመለስ ከ6-12 ወራት መዉሰድ ይኖርበታል፡፡

ፕሮስታግላንዲን አናሎግ

እነዚህ መድሃኒቶች ፀጉር እንዲያድግ የሚያደርግ ሲሆን ገና በጥናት ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህ መካከል ቢማቶፕሮስት/ ለቅንድብና ለአይን ሽፋን ፀጉር የሚስተካከለው የለም፡፡

ሎሚጋን

ይህ መድሃኒት ለግላኮማ የሚታዘዝ ሲሆን እንዴት እንደሚሰራ ባይታወቅም ለፀጉር ዕድገት ውጤታማ ነው፡፡ የአይን ሽፋን ፀጉሮች ጠንካራና ረጂም እንዲሆን ያደርጋል፡፡
(በዶክተር ቤዛ አያሌው)

©t.me/jossiale2022

This Post Has One Comment

  1. Tadios

    መልሱ ተመችቶኛል !!!👍❤

Leave a Reply