ኒውዚላንድ ያለ ማህበረሰብ ውስጥ ስርጭት ድፍን 100 ቀናትን አስቆጥራለች::
የኒውዚላንድ ጤና ሚኒስቴር እንደተናገሩት በእሁድ ቀን ምንም የኮቪድ-19 አዲስ ታማሚ በሀገሪቱ አልተገኘም:: በሀገሪቱ ውስጥ በአሁኑ ሰአት ኮቪድ-19 ያለባቸው አጠቃላይ ሰዎች ብዛትም 23 ሲሆን ሁሉም በለይቶ ማቆያ ውስጥ ይገኛሉ::
በሀገሪቷ ውስጥ በሽታው ከያዘው ሰው ጋር የንክኪ ታሪክ ያልነበረው አዲስ ታማሚ ከተገኘ ድፍን 100 ቀናት ተቆጥረዋል:: ነገር ግን የሀገሪቱ የጤና ዳይሪክተር ጀነራል ዶክተር አሽሊ ብሉምፊልድ ለስኬቱ እውቅና ቢሰጡም አሁንም ግን ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል:: አክለውም በሌሎች የቫይረሱን ስርጭት በተቆጣጠሩ ሀገራት ቫይረሱ እንደገና በምን ያህል ፍጥነት ሊያንሰራራ እንደሚችል ስላየን ወደፊት ተጨማሪ ኬዞችን እንዳናገኝ መጠንቀቅ አለብን ብለዋል::
ከዚህ ቀደም ኮቪድ-19 ድል መንሳቷን አውጃ የነበረችው ኒውዚላድ ተጨማሪ 2 አዲስ የኮሮናቫይረስ ተጠቂዎችን ከአዋጁ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ማግኘቷን ይታወሳል::
ያገኘቻቸው 2ቱም የቫይረሱ ተጠቂዎች ከእንግሊዝ ወደ ኒውዚላንድ ያቀኑ ሲሆን የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ለመታደም በልዩ ፍቃድ ወደ ሀገሪቱ የገቡ ነበሩ፡፡